አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዲጅታል ሽግግር ሁሉንም ዜጎች ዘመናዊ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግና አካታች ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስችል መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ተደራሽነት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡
በኢንተርኔት ሶሳይቲ የተሰናዳውና በኢጋድ አባል ሀገራት የኢንተርኔት መሰረተ ልማትን ማሳደግ ላይ ያተኮረው የኢንተርኔት ልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በዲጅታል 2025 ስትራቴጂ መሰረት የዲጅታል ሽግግርን እውን የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቴሌኮም መሰረተ ልማትን በከፍተኛ ሁኔታ እያስፋፋችና እያዘመነች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የ4 ጂ ኔትወርክ ተደራሽነት ሀገራዊ ሽፋን 34 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን አንስተዋል።
5 ጂ ኔትወርክም በትላልቅ ከተሞች አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው፥ ይህም የኢንተርኔት ተደራሽነትንና ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ነው ያሉት።
ኢትዮ ቴሌኮም የጀመረው ቴሌ ብር ከ51 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን በማፍራት አካታች የዲጅታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የግል የቴሌኮም ኦፕሬተሮችና የዳታ ማዕከል አቅራቢዎች በሀገሪቱ እንዲሰማሩ በማድረግ ዲጅታል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ አሻራቸውንን እያሳረፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጅታል ሽግግር ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ አገልግሎትና አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባትና በአፍሪካ የዲጅታል አብዮት መሪ እንድትሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።
ለሦስት ቀናት የሚቆየው የኢንተርኔት ልማት ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በሌሎች የኢጋድ አባል ሀገራት የኢንተርኔት መሠረተ ልማቶችን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ እንዳሉት፤ የኢንተርኔት ጉባኤ በኢጋድ አባል አገራት የኢንተርኔት ተግዳሮቶችን መፍታት፤ የእውቀት ሽግግር፤ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም የበይነ መረብ ትስስርን ማጎልበትን ያለመ ነው።
የኢንተርኔት ልማት ላይ ተፅእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ቁልፍ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሄዎች መስጠት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡
የኢንተርኔት ሶሳይቲ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አስራት ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢንተርኔት የፈጠራ አቅም እንዲጎለብት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድህነትን ለማስወገድና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማሳካት ለኢንተርኔት መሰረተ ልማት መስፋፋት ትኩረት መስጠቷንም ነው የጠቆሙት፡፡
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025