አዲስ አበባ፤የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፦የኮሪደር ልማቱ መዲናዋን ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ መዳረሻነት ከመቀየር ባለፈ ይበልጥ የትኩረት ማዕከል እንድትሆን ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት የመንግሥትና የፓርቲ አፈፃፀም ግምገማ ተጠናቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት፥የከተማ አስተዳደሩ አፈጻጸም የሚገመገመው ለህዝብ የገባነውን ቃል እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዳችንን ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ለውጥ ሂደት ቢሆንም በሁሉም መመዘኛዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ሰው ተኮር ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ፣የአፍሪካውያንና ዓለም አቀፋዊ ሀላፊነት ያለባት ከተማ መሆኗን የገለጹት ከንቲባዋ፤በስድስት ወራት ውስጥ የሚታይና የሚጨበጡ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማት አዲስ አበባ ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ መዳረሻነት ከመቀየር ባለፈ የዓለም የትኩረት ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል፡፡
በወንዞች ዳርቻ በተከናወነ ሥራ የወንዞችን መዓዛ መቀየር ጀምረናል ነው ያሉት፡፡
የኮሪደር ልማት የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ነዋሪዎች ማህበራዊ ትስስራቸው ተጠብቆ ከደሳሳ ጎጆ ወጥተው ደረጃውን ወደጠበቀ ቤት እንዲገቡ አስችሏል ብለዋል፡፡
የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ "መፍጠርና መፍጠን" ባህላችን ሊሆን ይገባል ሲባል በተመሳሳይ ጊዜና በጀት ወጥ አፈጻጸም ማስመዝገብ ጭምር መሆኑን አንስተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለህዝቡ ቃል በገባው መሰረት የኑሮ ጫናን መቀነስ የሚያስችሉ ሰው ተኮር ሥራዎችን በብቃት መፈፀም ችሏል ብለዋል፡፡
በመዲናዋ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ በመመገብና የትምህርት ቤት ወጪያቸውን በመሸፈን ትውልድ ላይ አበክረን እየሰራን ነው ያሉት ከንቲባዋ።
የኢትዮጵያ ገበሬዎች በአዲስ አበባ የገበያ ማዕከላት ምርታቸውን በመሸጥ የድካማቸውን ዋጋ የሚያገኙበት እድል ፈጥረናል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፥ በመዲናዋ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ መስጠት እንደተጀመረ ገልጸው፥ ከነዋሪዎች ፍላጎትና ከተማዋ መድረስ ከሚገባት የከፍታ ደረጃ አንፃር ብዙ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ከነዋሪዎች ጋር በመተባበር በትራንስፖርት እና መሰል አገልግሎቶችና የመሰረተ ልማት ግንባታ ልማት በርብርብ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ፥ በመዲናዋ በተከናወኑ የልማት ስራዎች የተመዘገበው ውጤት ከነዋሪዎችም አልፎ ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዘውን ውጥን ለማሳካት በሁሉም ዘርፎች ከዚህ በላይ የተቀናጀ የአመራር ጥረት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025