የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

<p>ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መረጋገጥና የንግድ ልውውጥ ማደግ አበክራ እየሰራች ነው - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)</p>

Feb 13, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መረጋገጥና የንግድ ልውውጥ ማደግ አበክራ እየሰራች መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።

"ከቪዛ- ነጻ እንቅስቃሴ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን" በሚል መሪ ሃሳብ የአፍሪካ ሚኒስትሮች ስትራቴጂካዊ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) የአፍሪካ ህብረትና የአፍሪካ ልማት ባንክ አመራሮች እንዲሁም ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ትስስር እንዲጠናከር በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች፡፡


እንዲሁም ገበያዎቿን ለአፍሪካ ሀገራት ክፍት በማድረግ በሀገራት መካከል ያለው የንግድ ትስስር እንዲጠናከር በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝም ነው ያነሱት፡፡

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለአህጉራዊ የንግድ ትስስር መሳለጥ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ናትም ብለዋል።

በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የሙከራ ንግድ ለመጀመር ዝግጅቷን ማጠናቀቋም በአህጉሪቱ ያለው የንግድ ልውውጥ የተቀላጠፈ እንዲሆን ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ በፓንአፍሪካዊ እሳቤ ታሪካዊ ሚና መወጣቷን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ በዚህም የአፍሪካውያን የነጻነት ቀንዲል ሆናለች ብለዋል።

አፍሪካውያን በዚህ ዘመን የእርስ በርስ ትስስራቸው እንዲጎለብት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን እንዲያረጋግጡና በአህጉሪቱ የንግድ ልውውጥ እንዲጠናከር ታሪካዊ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑንም ገልጸዋል።


በአፍሪካ ህብረት የሠራተኞች፣ የሥራ ቅጥርና የስደተኞች ዘርፍ ኃላፊ ሳቤሎ ምቦካዚ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የአፍሪካውያን ከቪዛ ነጻ ዝውውር እውን መሆን አፍሪካ ላሰበችው የነጻ ቀጣና ኢኮኖሚ ትስስር ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

ህብረቱ ከቪዛ ነጻ እንቅስቃሴን እንዲያጠናክሩ በትኩረት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።


የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ኒና ንዋቡፎ፥ አፍሪካ በተፈለገው ደረጃ የነጻ ቪዛ እንቅስቃሴን መተግበር አለመቻሏ ኢኮኖሚዋ እንዳያድግ ማነቆ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ከቪዛ ነጻ እንቅስቃሴን በመፍቀድ አህጉራዊ ኢኮኖሚንና የንግድ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንደሚቻል ነው የጠቆሙት።

ከቪዛ ነጻ እንቅስቃሴ የአፍሪካ ኢኮኖሚን በከፍተኛ ሁኔታ ከማሳደጉ በተጨማሪ የስራ እድልን የሚያሰፋ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አባል ሀገራት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.