ጂንካ፤ የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፡- በጂንካ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ውብ፣ ጽዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረጉን አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን በቱሪስቶች ተመራጭ እንድትሆን እያደረጋት መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ሀብታሙ ወልዴ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱ ጂንካ ከተማን ውብና ፅዱ በማድረግ ገጽታዋን እየቀየረ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
የኮሪደር ልማት ለከተማዋ ፈጣን እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ታደሰ ናቸው።
ከዚህ ቀደም የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ጠባብ በመሆናቸው የትራፊክ አደጋ በተደጋጋሚ ይከሰት እንደነበር አስታውሰው፣ በኮሪደር ልማቱ ከመንገድ ግራና ቀኝ የተሰራው የእግረኞች መንገድ አደጋውን ይቀንሰዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጹት ደግሞ አቶ ግርማ ተካልኝ እና ወጣት ምጥን ተፈራ የተባሉ አስተያየት ሰጪዎች ናቸው።
ልማቱ ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸው፣ በልማቱ የከተማዋ ገጽታ እየተለወጠ መምጣቱን ተናግረዋል።
በጂንካ ከተማ በንግድ ስራ ላይ የተሰማራችው ወጣት ምጥን ተፈራ፣ በአካባቢዋ የኮሪደር ልማት ሥራ ከመከናወኑ በፊት ከመንገድ ላይ የሚነሳው አቧራ የደንበኞቿን ምቾት ይነሳ እንደነበር አስታውሳለች።
በዚህም የዕለት ገቢዋ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ እንደነበር ገልጻ፣ የኮሪደር ልማቱ ይህን ችግር እንደፈታላት ተናግራለች።
ከዚህ ቀደም የከተማዋ ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት የመዝናኛ ስፍራ በበቂ ሁኔታ እንዳልነበር የተናገረው ወጣት አረቡ ሰኢድ በበኩሉ፣ ልማቱ አማራጭ የመዝናኛ ስፍራዎች መፍጠሩን ገልጿል።
በተጨማሪም የጋራ ስፖርት መስሪያ እና ውድድሮች የሚያካሂዱባቸው ምቹ ስፍራዎች እንዲኖረው ተደርጎ መከናወኑንም ተናግሯል።
የጂንካ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ማርቆስ ኃይሌ በከተማው በመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ለልማቱ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ጠቅሰው፣ የልማት ሥራው የእግረኛ መተላለፊያ መንገዶች፣ የአደባባይ ልማት፣ ፋውንቴን እንዲሁም የመንገድ ዳርና የመንገድ አካፋይ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች መካተታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ጂንካ ከተማን ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ተመራጭ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ ለልማቱ የከተማው ማህበረሰብ ያልተቆጠበ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025