የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

<p>በመዲናዋ በረጅም ጊዜ ክፍያ የማምረቻ ማሽን ያገኙ ስራ ፈጣሪዎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል</p>

Feb 14, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ በረጅም ጊዜ ክፍያ የማምረቻ ማሽን ያገኙ ስራ ፈጣሪዎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር በማስያዣ የመስሪያ ማሽን ማግኘት ለማይችሉ ተቋማት ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

ማህበሩ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸውን የማምረቻ ማሽን አቅርቦት ችግር ለመፍታት የዱቤ ኪራይ ግዥ አሰራር በመዘርጋት ለሀገራዊ ልማት እገዛ እያደረገ ይገኛል።

የመስሪያ ማሽን በዱቤ ኪራይ አግኝተው ወደ ሥራ የገቡ አንቀሳቃሾች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተደረገላቸው ድጋፍ ከራሳቸው አልፈው ወገኖቻቸውን መጥቀም ችለዋል፡፡

ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክት ምህንድስና የተመረቁት እህትማማቾች የመሰረቱት የትንሳኤና ጓደኞቻቸው የእንጨት ስራ ማህበር በዚህ ረገድ ለሴቶች አርአያ የሚሆን ስኬት አስመዝግቧል፡፡


የማህበሩ መስራችና ባለቤት ወጣት ትንሳኤ ዳዳ ማህበሩ ከተመሰረተ ሶስት አመት እንደሞላው አስታውሳ ከአዲስ ካፒታል በወሰዱት ማሽን ታግዘው ለስኬት መብቃታቸውን ተናግራለች፡፡

እህትማማቾቹ በንድፈ ሃሳብ በተማሩትና ተቀጣሪ ሆነው ሲሰሩ ባገኙት ልምድ በመታገዝ ያስመዘገቡት ውጤት ለዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች በተለይ ደግሞ ለሴቶች አርአያ የሚሆን ነው፡፡

አሁን ላይ ከራሳቸው አልፈው ለአምስት ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን በመግለጽ የወሰዷቸውን የማሽን ብድሮች በመክፈል ሁለት ሚሊየን ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን ተናግራለች፡፡


የካሳየ እና በለጠ ብረታ ብረት ህብረት ሽርክና ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ በለጠ ብርሃኑ በበኩላቸው ከአዲስ ካፒታል ፋይናንስ በብድር በወሰዱት ማሽን ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ በሚያደርግላቸው ድጋፍ እና ክትትል ውጤታማ መሆናቸውን በመግለጽ፤ አሁን ላይ ለ22 ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡


ከአዲስ ካፒታል በብድር ማሽን በመውሰድ በተኪ ምርት ላይ የተሰማሩት አቶ መርእድ አበበ በስኬታቸው አርአያ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለተኪ ምርት የሰጠው ልዩ ትኩረት ትልቅ እድል ይዞላቸው እንደመጣ ያስረዳሉ፡፡

ከማህበሩ በወሰዱት 40 ሺህ ብር የሚያወጣ ማሽን የጀመሩት ስራ ውጤታማ በመሆኑ ካፒታላቸው 12 ሚሊየን ብር መድረሱንና 30 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግሯል፡፡


በማህበራቱ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች በበኩላቸው በተፈጠረላቸው የስራ አድል ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን እያገዙ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የማህበሩ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ጸጋየ ሽምብር በበኩላቸው ማህበሩ ከተቋቋመ አንስቶ በርካታ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል፡፡


በዚህም ከ5 ሺህ 700 በላይ ኢንተርፕራይዞች የማህበሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን በመግለጽ ለ26 ሺህ ዜጎች ደግሞ የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የመስሪያ ማሽን ብድር አገልግሎት እንዲሰጥ በከተማ አስተዳደሩ ተቋቁሞ በመስራት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.