የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

<p>በኢትዮጵያ የተመድ የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት የአፍሪካ ቢሮ መከፈቱ በዓለም ሁነቶች ላይ ያላትን የነቃ ተሳትፎ የሚያሳይ ነው</p>

Feb 18, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤የካቲት 10/2017(ኢዜአ)፦የተመድ የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት የአፍሪካ ቢሮ በኢትዮጵያ መከፈቱ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ላይ ያላትን የነቃ ተሳትፎ የሚያሳይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መክፈቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡


በመርሃ ግብሩ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የተመድ የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡


የተመድ የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት በዓለም ዙሪያ ያሉ የፈጠራ ልሂቃንና የቴክኒክ ባለሙያዎችን የሚያሰባስብ ነው፡፡


የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሁሉን አቀፍ ሪፎርም አድርጋለች፡፡


የኢትዮጵያ የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጥ መዳረሻውን ብልጽግና ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች አካታች ሪፎርም መደረጉን ገልጸው፥ ኢትዮጵያ የዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቧን ጠቅሰዋል፡፡


በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ህዝብና ኢኮኖሚ የላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፥ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ምስረታና አበርክቶ የጎላ ሚና እንዳላትም ገልጸዋል፡፡


የተመድ የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት የአፍሪካ ቢሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መከፈትም ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁነቶች ያላትን የነቃ ተሳትፎ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ በሚያስችል ቁመና ላይ የተመሰረተ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ግቡን ለማሳካት የተለያዩ የፖሊሲ ርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል፡፡


የውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማዘመን፣ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ማሻሻል ትኩረት የተደረገባቸው እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡


የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ግብርና ቱሪዝምና ማዕድን የመንግስት የትኩረት መስኮች መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ የመንግስት የዲጂታል አገልግሎትና ዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡


መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስፋፋትና የተሟላ መሰረተ ልማት በማቅረብ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያድግ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.