የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

<p>ምሩቃን በሰለጠኑበት ሙያ የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል</p>

Feb 24, 2025

IDOPRESS

ወላይታ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- ምሩቃን በሰለጠኑበት ሙያ የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና(ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 524 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።


በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ እንደ ሀገር ብልጽግናን ለማረጋገጥና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናከር በየመስኩ ብቁ የሰለጠነ የሰው ሀይል ያስፈልጋል።

በመሆኑም ምሩቃን በሰለጠኑበት ሙያ ምርምር በማድረግና በአዳዲስ እሳቤዎች የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክረው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

በተለይ የአርሶ አደሩን ባህላዊ የአመራረት ዘይቤ በመቀየር ውጤታማ ለማድረግ በቅርበት ሆነው መስራት እንዳለባቸውም አመልክትዋል።

ሀገር ወደ ተሻለ ደረጃ እንድትደርስ የመቻቻል፣ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበትና ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።


የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ጉቼ ጉሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ መስኮች በዕውቀትና በክህሎት የሰለጠነ የሰው ሀይል እያፈራ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ምርምሮች እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን ማከናወኑንም ገልጸዋል።

የዛሬ ተመራቂዎችም በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው በቀጣይ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል።

በሦስተኛ ዲግሪ የተመረቁት ተገኝ ሀይሉ(ዶ/ር) በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባገኙት እውቀት ሀገርና ህዝብን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዛሬ ምሩቃን መካከል 737ቱ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በወላይታ ሶዶና ታርጫ ካምፓሶች በመደበኛ፣ በማታ፣ በእረፍት ቀናትና በርቀት የትምህርት መርሀግብሮች 39 ሺህ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.