የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

<p>በፓርቲው አቅጣጫዎች መሰረት ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ይሠራል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ</p>

Feb 24, 2025

IDOPRESS

አርባ ምንጭ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ አቅጣጫዎች መሠረት ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ አተኩሮ በአርባ ምንጭ ከተማ የተካሄደው ህዝባዊ ኮንፍረንስ ተጠናቋል።

በውይይቱ ላይ የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሁለንተናዊ የልማት ዘርፎች በተከናወኑ ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የማዕድን ሀብት በስፋት ቢኖርም ኢንዱስትሪ ፓርክና ፋብሪካዎች ባለመኖራቸው ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ አንስተዋል።


አርባምንጭ ከተማን ከጫሞና አባያ ሐይቆች ጋር የሚያስተሳስር የትራንስፖርት ልማት፣ እንዲሁም የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ህልውና ላይ የተደቀነውን ሰው ሠራሽ አደጋ ለመግታት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ከነዳጅ አቅርቦትና ግብይት ጋር በተያያዘ እየተበራከተ የመጣው ህገ-ወጥነትና ፍትሃዊ የስርጭት ችግር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑንም አንስተዋል።

መድረኩን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም በብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሰረት ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ፓርቲው ባለፉት ሦስት ዓመታት በሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሥራዎች ማከናወኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ውጤታማ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በአርባ ምንጭና አካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በአግሮ ኢንዱስትሪና በፋብሪካ ግንባታ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

የአካባቢው ህዝብ ለሰላም ያለው ትርጉም ከፍተኛ በመሆኑ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ገልጸው፣ የአካባቢውን የልማት ጸጋ በመጠቀም ከድህነት ለመውጣት መስራት ይገባል ነው ያሉት።


ከነዳጅ ግብይት ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥነት በማጋለጥ ህዝቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆምም ከንቲባ አዳነች ጠይቀዋል።

የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ሰፊ ዕቅዶችን ነድፎ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሠረተ ልማትና በማዕድን ዘርፍ ቀጣናውን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ሥራዎች ትኩረት መስጠቱንም አመልክተዋል።

በአርባምንጭና አካባቢው ያለው ሰላም ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ልማት መነቃቃት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመታደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡

አርባምንጭ ከተማን ጨምሮ በክልሉ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

ሰላምና ልማትን በማደናቀፍ የህዝብን የአንድነት እሴቶች ለመናድ የሚቃጡ የጥፋት ሀይሎችን በማጋለጥ ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.