አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፦ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያን ምርቶች ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ስራን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
ኢትዮጵያ በርካታ ምርቶችን ለውጭ ገበያ እያቀረበች ብትገኝም ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር የሚገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑ ይነገራል።
በመሆኑም ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ምርቶቿ ዓለም አቀፍ እውቅና ኖሯቸው ተወዳዳሪነታቸው እንዲጨምር የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የህግ ባለሙያና የንግድ ምልክት ወኪል ሰላማዊት ዓለማየሁ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በመልክዓ ምድራዊ አመላካች ሊጠበቁ የሚችሉ በርካታ ምርቶች ቢኖሩም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙት ግን ጥቂቶች ናቸው።
"መልክዓ ምድራዊ አመላካች" የሚባለው የአንድ አካባቢ ምርት ባለው ልዩ ጥራት፣ ዝና፣ ተቀባይነትና ተመራጭነት ሲኖረው ነው ያሉት ባለሙያዋ፥ ምርቶቹ የአዕምሯዊ ጥበቃ ሲደረግላቸው የኢኮኖሚ ጠቀሜታቸው የጎላ ይሆናል ብለዋል።
የይርጋጨፌ፣ ሐረርና ሲዳማ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘታቸው ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።
ሌሎች ምርቶችም በመልክዓ ምድራዊ አመላካች ምዝገባና ጥበቃ እንዲደረግላቸው በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ የአካባቢውና የሀገርን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለምታከናውነው ተግባር አጋዥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዳሉ ሞሲሳ ፥ ባለስልጣኑ አዕምሯዊ ንብረት ጠንካራ የህግ ጥበቃ እንዲያገኝ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለመንግስት እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ምርቶች የታደለች ብትሆንም እነዚህን ምርቶች በቦታቸው፣ በጥራታቸውና በልዩ ባህሪያቸው የመልክዓ ምድራዊ አመላካች ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዳልነበረ አውስተዋል።
አሁን ላይ የህግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሀገር ደረጃ የተመዘገቡ የቡና ምርቶችን በመልክዓ ምድራዊ አመላካች እንዲካተቱና ኢትዮጵያን ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ የሚሰራውን ተግባር ሁሉም ሊደግፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025