ሽሬእንዳስላሴ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል አደገኛ ኬሚካሎችን በመጠቀም የሚካሄድ ህገ-ወጥ የወርቅ ማምረት ሥራ በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሃብት ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የደለል ወርቅ ክምችት ባለባቸው ወረዳዎች ከሚኖሩት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች፤ በህገ ወጥ የወርቅ አምራቾች አካባቢው እየተጎዳና በሰዎች ላይም የጤና እክል እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ከነዋሪ አርሶ አደሮቹ መካከል በዞኑ በሰየምቲ አዲያቦ ወረዳ የ''ምድረ ፈላሲ'' የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የዕብዮ ደብረፅዮን ምክንያቱ በውል በማያውቁት ምክንያት 15 ፍየሎቻቸው እንደሞቱባቸው ገልጸዋል።
የፍየሎቻቸው የሞት መንስኤ የሚጠጡት ውኃ ህገ-ወጥ የወርቅ አምራቾች በሚጠቀሙት ኬሚካል የተበከለ በመሆኑ መከሰቱን ቆይተው መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
የዚሁ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ንጉሰ ምራጭ በበኩላቸው፣ ባልተለመደ ሁኔታ የጥጃዎች ሞቶ መወለድና የላሞች እርግዝና መጨናገፍ መበራከቱን አስረድተዋል።
በህገ-ወጥ የማዕድን አውጪዎች ምክንያት በዘፈቀደ የሚቆፈሩ ጉድጓዶች በግብርና ስራቸው ላይ እክል መፍጠሩን የገለፁት ደግሞ በዞኑ አስገደ ወረዳ የ''ሜሊ'' ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አሰፋ የማነ ናቸው።
እንዲሁም ህገ-ወጥ የወርቅ አምራቾቹ በአካባቢያቸው የሚገኝ ወራጅ ወንዝ በባዕድ ነገር በመበከላቸው ያረቧቸው የነበሩ እንስሳት እንደሞቱባቸው ተናግረዋል።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሽሬ ካምፓስ አስተባባሪ ዳዊት ማሞ (ዶ/ር) በካምፓሱ የማዕድን ፋካሊቲ ምሁራን ባደረጉት ጥናት ለህገ-ወጥ ወርቅ የማውጣት ተግባር እየዋለ ያለው ኬሚካል በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አረጋግጠዋል ብለዋል።
በተለይ ሜርኩሪና ሲያናይድ የተባሉ አደገኛ ኬሚካሎችን ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ በመጠቀም ወርቅ በሚመረቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወራጅ ወንዞችን መበከላቸውን አመልክተዋል።
ይህንን ተከትሎም በተለይ በእንስሳት ላይ የሞት አደጋ መከሰቱን በተደረገው ጥናት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
እንዲሁም ህገ-ወጥ በሆነ የወርቅ ማምረት ስራ እዚህም እዛም ጉድጎዶችን በመቆፈር ለም አፈር እንዲሸረሸር እንዲሁም ደን እንዲወድም እያደረገ መሆኑንም በጥናቱ መረጋገጡን አስረድተዋል።
በዞኑ እየተስተዋለ ያለው ህገ-ወጥ የማዕድን ማውጣት ተግባር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እያመዘነ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የማእድን ፋካሊቲ ዲን አቶ በረከት ገብረስላሴ ናቸው።
እንደ እሳቸው ገለፃ የሚመለከተው አካል ህገ-ወጥ ድርጊቱን በተቀናጀ መልኩ ሊከላከል እንደሚገባም አፅንዖት በመስጠት አመልክተዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025