የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

ለሀገራዊ ብልፅግና ወሳኝ አቅም ያለውን የአማራ ክልል ግብርና ማዘመን ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

Mar 11, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2017(ኢዜአ)፦ለሀገራዊ ብልፅግና ወሳኝ አቅም ያለውን የአማራ ክልል ግብርና ማዘመንና ማሸጋገር እንደሚገባ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን የ10 ዓመት መነሻ ዕቅድ ላይ ከምሁራንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በባህርዳር ምክክር አካሄደዋል።

በምክክር መድረኩ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በምክክሩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሀገራዊ ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሀገራዊ አቅምን፣ ሀገር በቀል የፖሊሲ ዕይታና የትግበራ ሂደት ታሳቢ ተደርጓል ብለዋል፡፡

መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የዕድገት ምሰሶዎች ብሎ ከለያቸው አምስት ዘርፎች አንዱ ግብርና መሆኑንም ጠቅሰዋል።


ኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን እየሠራች መሆኑን ገልጸው፤ ለግቡ መሳካት የአማራ ክልል ግብርና ልማት ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል በቅኝ ባለመገዛት የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን አውስተው፤ አፍሪካውያን ያላቸውን እምቅ ጸጋ ተጠቅመው ራሳቸውን እንዲችሉ አርዓያነት ያለው ሥራ እያከናወነች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በቀጣይ አምስት ዓመታት በኢኮኖሚው መስክ በራስ የመልማት አቅምን በመጠቀም ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችል ዳግማዊ ዓድዋን በልማት ለመድገም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን በአግባቡ አዳብሮ ወደ ትግበራ ማስገባት ሀገራዊ ግቡን ለማሳካት የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ታታሪ አርሶ አደሮች፣ ሰፊ የሚታረስና ለም መሬት፣ እምቅ የውሃ አቅም ያለው በመሆኑ ዘርፉን በሜካናይዜሽንና በግብዓት አቅርቦት በማሳደግ ጥቅሙን ማጎልበት ይገባል ብለዋል፡፡


በመሆኑም የክልሉን የግብርና አቅም ለማባዛት የሥራና የባህል ለውጥ በማምጣት ሁሉም መረባረብ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት የተጀመረው ጉዞ የላብ ዋጋ የሚፈልግ በመሆኑ ተነሳሽነት ሊኖረን ይገባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሀገራዊ ብልጽግና ወሳኝ ሚና ያለውን የክልሉን ግብርና ማዘመን፣ ማሸጋገር እና በዕቅድ መመራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ኑሮውን የሚመራበት፣ ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበትና ለሌሎችም የልማት ሥራዎች መሰረት በመሆኑ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ዘርፉን ካለበት ልማዳዊ አሰራር በማላቀቅ ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በፍጥነት አጠናቅቆ በቁጭት ወደ ሥራ ማስገባት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመነሻ ዕቅዱ ባለፉት ስድስት ወራት በግብርና ሚኒስቴር፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና በክልሉ መንግሥት በጋራ ሲዘጋጅ የቆየ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.