የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

የሐይቅ-ቢስቲማ-ጭፍራ አስፋልት መንገድ ግንባታን ለማፋጠን በቅንጅት እየተሰራ ነው

Mar 11, 2025

IDOPRESS

ደሴ፤ መጋቢት 1/2017(ኢዜአ)፡- የሐይቅ-ቢስቲማ-ጭፍራ አስፋልት መንገድ ግንባታን በማፋጠን በጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

የመንገዱ ግንባታ ያለበትን ሁኔታ የአማራ ክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራር አባላት ዛሬ ጎብኝተዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ተስፋዬ አንተንይስሙ እንደገለጹት፤ የመንገዱን ግንባታ በጥራት በማከናወነ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ ነው፡፡

ሆኖም የወሰን ማስከበር፣ የውሃ መስመር ዝርጋታና ሌሎች ያጋጠሙ ጥቃቅን ክፍተቶችን ለማስተካከል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


ይህም ጥረት ከክልሉ፣ ከደቡብ ወሎ ዞንና ከአካባቢው አመራር አባላትና ህብረተሰቡ ጋር በመነጋገር መሆኑን አስረድተዋል፡፡


የሐይቅ-ቢስቲማ-ጭፍራ የአስፋልት መንገድ የፕሮጀክት ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጅነር ፀጋ ፈንታሁን በበኩላቸው፤ 74 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ግንባታ ሥራ ለማፋጠን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ የመንገዱ ግንባታ አጠቃላይ አፈጻጸም 39 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ግንባታው በጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ እየተደረገ ባለው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።


የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የመሰረት ልማት አማካሪ አቶ ደሴ አሰሜ በጉብኝቱ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ ነው።

ከሐይቅ-ቢስቲማ-ጭፍራ የአስፋልት መንገድ ግንባታ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ወሰን ማስከበርና ሌሎች ያጋጠሙ ጥቃቅን ክፍተቶችን ለማስተካከል እንደሚሰራም አስረድተዋል።


የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ በበኩላቸው፤ የመንገዱ ግንባታ አፈጻጸም በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ግንባታው በጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ህብረተሰቡ የበኩሉን ተሳትፎ እንዲያጠናክር መልዕክት አስተላልፈዋል።


ህብረተሰቡን በማወያየትና በማሳመን መንገዱ የሚያልፍበትን ቦታ ከሶስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ሐሰን ናቸው።

በጉብኝቱ የክልል፣ የደቡብ ወሎ ዞንና የሐይቅ ከተማ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.