አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ቢሾፍቱ አቅራቢያ አቡሴራ አካባቢ አዲስ ለሚገነባው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የፍላጎት መግለጫ ስምምነት ሰነድ ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የተፈራሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የቀጣናዊ ልማት፣ ትስስር እና ስትራቴጂ ምክትል ፕሬዝዳንት ኔና ንዋቡፎ ናቸው።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና (ዶ/ር) እና የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ተገኝተዋል።
7 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ የሚገመተው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ የሚገነባ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል ተብሎም ይጠበቃል።
አየር ማረፊያው በአገር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ለመወጣው የመንገደኞች እና የካርጎ አገልግሎቶች ፍላጎት በአጥጋቢ ሁኔታ ምላሽ ይሰጣል ነው የተባለው።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና (ዶ/ር) ጋር የተወያዩ ሲሆን በውይይታቸውም ሚኒስትሩ የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ልማት እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አድንቀዋል።
ባንኩ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በቁልፍ መስኮች ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገንዘብ ፈሰስ ማድረጉን አመልክተዋል።
ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ለባንኩ ፕሬዝዳንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት እየተተገበረ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ጠንካራ ሁሉን አቀፍ ዕድገት በማስመዝገብ ሁሉንም ዜጋ ተጠቀሚ ማድረግን ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
ባንኩ ለአየር መንገዱ ፕሮጀክት ከፈጠረው አጋርነት በተጨማሪ ለማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ቀጣናዊ ትስስር እና የታዳሽ ኃይል ልማትን ጨምሮ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና (ዶ/ር) የአፍሪካ ግዙፍ ፕሮጀክት የሆነውን የአዲሱን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ባንኩ ለመደገፍ ቁርጠኛ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያ ያስመዘገብችውን የ8 ነጥብ 1 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ሀገራዊ ለውጥ አድንቀው፤ የአዲስ አበባን ፈጣንና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያዊ ባለፈ ቀጣናዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ያላቸውን ጠንካራ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ለማላቅ መስማማታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025