የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

የንግዱ ማህበረሰብ መንግሥት የፈጠረውን ምቹ ዕድል እና እምቅ የመልማት አቅም መጠቀም ይገባዋል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)

Mar 17, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2017(ኢዜአ)፡- የንግዱ ማህበረሰብ መንግሥት የፈጠረውን ምቹ ዕድል እና እምቅ የመልማት አቅም በመጠቀም የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንደሚገባው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።

14ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ግቡን በመምታት በስኬት መጠናቀቁን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና መርሀ ግብር ተካሂዷል።

የንግድ ትርዒቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን 300 የሚደርሱ የሀገራትና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል።


ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ 14ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ግቡን በመምታት በስኬት ተጠናቋል።

የንግድ ትርዒቱ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማስተዋወቅና ግብይት በመፈጸም በኩል ስኬታማ እንደነበርም አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ የንግድ ትርዒቱ የኢትዮጵያን ልክና መጠን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ መግለጥ የሚያስችል አውድ ፈጥሯል ነው ያሉት።


አያይዘውም ሚኒስቴሩ የንግዱን ማህበረሰብ የንግድ ፈቃድ በበይነ መረብ(ኦንላይን) በማደስና አዲስ በማውጣት ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስምንት ወራት 2 ነጥብ 3 ሚሊየን አዳዲስ ፈቃድ ማውጣት እና የእድሳት አገልግሎቶች መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ባለፉት ዓመታት ሲሰጥ ከነበረው አገልግሎት አንፃር በእጅጉ መሻሻሉን ገልጸው፣ ለንግዱ ማህበረሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት የበለጠ ለማሳለጥ አበክረን እንሰራለን ብለዋል።


መንግስት የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳደግ በወሰዳቸው የፖሊሲ እርምጃዎች ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስምንት ወራት ከምርት ኤክስፖርት ብቻ 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በአዲስ ከተደራጀ በኋላ ተስፋ ሰጭ ውጤት ቢያስመዘግብም ኢትዮጵያ ካላት አቅም አንፃር ከዚህ በላይ መስራት ይገባዋል ብለዋል።


የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ቀነኒሳ ለሚ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት የንግዱን ማህበረሰብ ተሳትፎ እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ በኋላ በተደረጉ የፖሊሲና የአስተዳደር እርምጃዎች የግሉ ዘርፍ መነቃቃት አሳይቷል ብለዋል።

በመካከለኛና አነስተኛ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.