የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

በባህር ዳር ከተማ 14 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ስራ ገቡ

Mar 18, 2025

IDOPRESS

ባህርዳር፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፦በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በግንባታ ላይ የነበሩ 14 ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመታገዝ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን የአስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።


በመምሪያው የኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ አቤል ኢሳኢያስ ለኢዜአ እንደገለፁት ወደ ማምረት የተሸጋገሩት ኢንዱስትሪዎች ከ592 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው።


ኢንዱስትሪዎቹ በኬሚካል፣ በሳሙና፣ በበቆሎ ስታርች፣ በፓስታ፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በእብነበረድ፣ በብረታ ብረትና በመኪና ፊልትሮ ማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው ብለዋል።


ባለድርሻ ተቋማትም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመመራት የመብራት፣ የውሃ፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማሟላታቸው ኢንዱስትሪዎቹ ፈጥነው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ማስቻሉን ገልጸዋል።


ኢንዱስትሪዎቹ ለ747 ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመው ግንባታቸውን ያጠናቀቁ 10 ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍም ወደ ማምረት ለማሸጋገር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


በከተማ አስተዳደሩ የዩኒክ ፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ ያዩ፤ በተደረገላቸው ድጋፍ ፋብሪካውን ወደ ማምረት ስራ እንዲገባ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።


አሁን ላይ ፋብሪካው በቀን እስከ 150 ኩንታል ፓስታ እያመረተ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልፀው በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲሸጋገር ወደ 400 ኩንታል የማሳደግ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።


የከተማ አስተዳደሩ የመብራት፣ የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲሟላ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው ለ122 ሰራተኞችም ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን አውስተዋል።


በከተማ አስተዳደሩ እስካሁን 342 አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በማምረት ስራ ላይ እንደሚገኙም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.