የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

ኢትዮጵያ በራዲየሽንና ኒውክሌር ቴክኖሎጂ ቁጥጥር የካበተ ልምድ አዳብራለች - ባለስልጣኑ

Mar 20, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በራዲየሽንና ኒውክሌር ቴክኖሎጂ ያካበተችውን ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት በተጨማሪ ቴክኖሎጂዎች ላይ ለመተግበር እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ገለፀ።

ባለስልጣኑ የፌደራል መንግስት አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ተጨማሪ ተግባርና ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

በዚህም የኒውክሌር እና የጨረራ አመንጭ መሳሪያዎችና ቁሶች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ፤ ከሀገር ሲወጡ፤ ጥቅም ላይ ሲውሉ፤ ሲጓጓዙ፤ ሲወገዱ፤ ሲዘዋወሩ፤ ሲከማቹ፣ የቁጥጥር፤ ህግ የማስፈጸም እና የክትትል ተግባራትን ያከናውናል፡፡

ባለስልጣኑ በተሰጠው ስልጣን ከዚህ ቀደም ከሚቆጣጠራቸው የጨረራና ኒውክሌር ቴክኖሎጂ በተጨማሪ አራት ቴክኖሎጂዎችን የመቆጣጠር ስራ እየሰራ ይገኛል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት ባለስልጣኑ ጨረር አመንጪዎችን የማሳወቅ፣ የፍቃድ አሰጣጥ፣ ኢንስፔክሽንና ህግ ማስፈፀም እንዲሁም በህግ ጥሰት ላይ እርምጃ የመውሰድ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል።

በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት በሁሉም ቴክኖሎጂዎች 2ሺህ 657 የተለያዩ ፈቃዶች ለመስጠት አቅዶ 2ሺህ 422 ፈቃድ መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሁሉም ቴክኖሎጂዎች 504 የኢንስፔክሽን ስራ እንዲሁም የማሳወቅና የመረጃ ምዝገባ ስራዎች መሰራታቸውንም አብራርተዋል።

በህክምና እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ የአገልግሎት ዘመንና የፕሮጀክት ጊዜያቸውን በጨረሱ ጨረራ አመንጪ ቁሶች ላይ የህግ ማስፈፀም ስራ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በተቋማቱ ላይ ከቀላል ማስጠንቀቂያ ጀምሮ የተለያዩ የህግ ማስፈፀም ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው አንድ ድርጅት በፍርድ ቤት ውሳኔ አገልግሎቱን የጨረሰ ቴክኖሎጂ ወደ መጣበት ሀገር እንዲመልስ መደረጉንም ገልፀዋል።

በራዲየሽንና ኒውክሌር ቴክኖሎጂ ላይ እየተከናወነ ያለውን ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ ለመድገም የህግ ዝግጅት መከናወኑን አስታውቀዋል።

ባለስልጣኑ የጨረራ ህክምና ምርምራ መስጫን ጨምሮ ጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች ያለ ፈቃድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመቆጣጠር ከጉምሩክ ኮሚሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.