የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

የፈጠራ ሃሳቦችን በስፋት ወደ ተግባር መለወጥ እንዲችሉ የሚደረገው ማበረታቻ መጠናከር አለበት - የፈጠራ ባለቤት ተማሪዎች

Mar 20, 2025

IDOPRESS

ባህርዳር፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ)፡- የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን በስፋት ወደ ተግባር በመለወጥ ለሀገር ጥቅም ማዋል እንዲችሉ የሚደረግላቸው የማበረታች ድጋፍ እንዲጠናከር በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ባለቤት ተማሪዎች ጠየቁ።

በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የወጣቶች የስራ ፈጠራ ውድድር ተሳታፊዎች መካከል በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት የማቴሪያል ሳይንስና ምህንድስና ተማሪ ዮሐንስ ይታይ አንዱ ነው።

ተማሪው ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት፤ የቀለም ማጣበቂያ ምርት(paint binder production) ከጓደኞቹ ጋር በመሆን መፍጠር እንደቻሉ ተናግሯል።

ውጤታማነቱ በቀለም ፋብሪካዎችና በዘርፉ ባለሙያዎች የተረጋገጠውን የፈጠራ ውጤት ሰሞኑን በተካሄደው ውድድር በማቅረብ 3ኛ በመውጣት ለሽልማት መብቃታቸውን ገልጿል።

ይህ የፈጠራ ውጤት እገዛ ተደርጎልን በስፋት ወደ ማምረትና ማከፋፈል ቢሸጋገር ምርቱን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት የሀገርን ኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን እንደሚያግዝ ጠቁሟል።

በዚህም ለሀገር ወስጥ ፍጆታ የሚውል በቂ ምርት ለማምረት ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት የመስሪያ ቦታና ብድር እንዲያመቻቹላቸው ጠይቋል።

ወጣቶች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች አበረታች ናቸው ያለችው ደግም በዩኒቨርሲቲው የ5ኛ ዓመት የኬሚካል ምህንድስና ተማሪና የፈጠራ ባለቤት እፁብ ድንቅ ቦሩ ናት።

አንድ የፈጠራ ስራ ችግር ፈቺነቱ የሚረጋገጠው በናሙና ደረጃ አዋጭ ሆኖ ስለተገኘ ብቻ ሳይሆን በስፋት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ መሆን ሲችል መሆኑን በመገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቃለች።

የፈጠራ ሥራ የራስን አቅም የመጠቀም ልምድን በማዳበር ለቀጣይ የምርምር ሥራ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የፈጠራ ባለቤት ተማሪዎቹ ጠቁመዋል።

በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የወጣቶች የስራ ፈጠራ ውድድር ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በመላው ኢትዮጵያ ፈጠራን በመደገፍና በማስተዋወቅ የሀገር በቀል ኢኮኖሚው እንዲበረታታ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

ለዚህም በየአካባቢው የሚወጡ የወጣቶች የፈጠራ ስራን በመደገፍ፣ በማበረታታትና ለውጤት እንዲበቃ በማድረግ ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት መፋጠን የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውም እንዲሁ።

በባህርዳር ከተማ ሰሞኑን የተካሄደውን የወጣቶች የስራ ፈጠራ ውድድር መዘገባችን የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.