የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

የመቀሌ ከተማን ውብና ፅዱ ለማድረግ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል

Apr 3, 2025

IDOPRESS

መቀሌ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፡- የመቀሌ ከተማን ውብና ፅዱ ለማድረግ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ ማኑፋክቸሪንግ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች ለኢዜአ እንዳሉት በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ከተማውን ፅዱና ውብ ለማድረግ ከ588 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል።


የመቀሌ ከተማ የማኑፋክችሪንግ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ልዕልቲ ፍስሃ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባሉት ሶስት ወራት 161 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠጠር የማልበስ እና 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ ደግሞ በኮብል ስቶን የማስዋብ ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

በኮብል ስቶን የማስዋብ ስራውና በሌሎች የልማት ተግባራትም በመቀሌ ከተማ የሚገኙ ሰባት ክፍለ ከተሞችን ውብና ፅዱ እንዲሆኑ እንደሚሰራ ገልፀው ወደ ተግባር ለመግባት ሲደረግ የቆየው ዝግጅት ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በ161 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ የማልበስ ሥራውም 15 የገጠር ቀበሌዎችን ከመቀሌ ጋር በማገናኘት ነዋሪዎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዚህ ስራም ለ4ሺህ 490 ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጠር ገልፀው ከተጠቀሱት ውስጥ 2ሺህ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።


ተግባሩን ለመከወን የተመለመሉና በ23 ማህበራት የተደራጁ ወጣቶች ስራውን በብቃትና በፍጥነት ለማከናወን የሚያስችላቸውን በተግባር የተደገፈ የሙያ ስልጠና መሰጠቱን የገለጹት ደግሞ የመቀሌ የኢንተርፕራይዝ ጥናትና ማቋቋም ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አለምሰገድ ገብረህይወት ናቸው።

በኮብል ስቶን ማስዋብ ስራና ሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ለመሰማራት የተደራጁት ወጣቶች የአካባቢያቸውን ልማት ከማፋጠን ባለፈ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግራቸውን ገቢ ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም ገልፀዋል።


በከተማው የሀድነት ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት መአርግ ሃይሉ በልማት ስራው ተሳትፋ ተጠቃሚ ለመሆን ተስፋ ማድረጓን ተናግራለች።


በከተማው የሃውልት ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት አብራሃም መብራህቱ በበኩሉ፣ ወጣቶች የተፈጠረውን ሰላም በመጠበቅ በልማት ራሳችንን ለመለወጥ መትጋት አለብን ብሏል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.