ደብረ ብርሃን፤መጋቢት 24/ 2017(ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል ምርታማነትን ይበልጥ በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የ2017/2018 የመኸር ሰብል ልማት እቅድን ለማሳካት በግብርና ፓኬጅ አተገባበር ላይ ያተኮረ ስልጠናና የእቅድ ትውውቅ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንዳመለከቱት፥በምግብ ራስን በመቻል የአገር ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።
ይህም የግብርና ምርትን በብዛትና በጥራት በማምረት በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂን በስፋት በመጠቀም መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ምርት ለምግብ ብቻ ሳይሆን ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃና ለኤክስፖርት የሚሆን በቂ ምርት ማምረት የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ይህንን ለማሳካትም በመካናይዜሽን፣በኩታ ገጠም አስተራረስ፣ በማዳበሪያ አጠቃቀምና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ አሰራሮችን መተግበር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂንና አሰራሮችን ተደራሽ ለማድረግም በክልሉ 50 የአርሶ አደር የምርምር ጣቢያዎች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ግንባታቸውን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመጪው ምርት ዘመን የታቀደውን ከ187 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማሳካት 8 ነጥብ ስምንት ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ የሚሳተፉ የዘርፉ አመራር አባላት ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም አርሶ አደሩን በግብርና ፓኬጆች ላይ በማሰልጠን፣ ተሞክሮ በማለዋወጥ እገዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አበበ ጌታቸው ፤በዞኑ በ2017/2018 የምርት ዘመን 556 ሺህ 491 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን መታቀዱን ተናግረዋል።
የዛሬው መድረክም አርሶ አደሩን በማንቃት የሚተገበሩ አሰራሮችን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
ከባሶና ወራና ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አረጋኸኝ ድንቅነህ በበኩላቸው፥አሲዳማ መሬትን ለማከም የሚያስችል ኖራ ለአርሶ አደሩ ቀርቦ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል 17 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው፥ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብአቶችም ወቅቱን ጠብቀው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በ2017/2018 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ አራት ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን የታቀደውን ግብ ለማሳካት ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025