የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቀጣናውን ሀገራት በጋራ የማደግ ራዕይ የሚያሳካ ፕሮጀክት ነው - አምባሳደር ነብያት ጌታቸው

Apr 7, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቀጣናውን ሀገራት በጋራ የማደግ ራዕይ የሚያሳካ ፕሮጀክት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ።

ቃል አቀባዩ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኩራት፥ ለአፍሪካውያን ደግሞ የይቻላል መንፈስን የፈጠረ ነው።


በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ድጋፍ በራስ አቅም እውን የሆነ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ በርካታ ፈተናዎች ማለፉን ያነሱት አምባሳደር ነብያት፥ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጫና ለመፍጠር የግድቡን ጉዳይ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ እንደወሰዱት አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ብስለት የተሞላበት የዲፕሎማሲ አካሄድን በመከተል መጠነ ሰፊ ጫናዎችን በመቋቋም ግድቡን አሁን የደረሰበት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንዲገኝ አድርገዋል ብለዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያውያን ህብረትና የፅናታቸው ውጤት እንደሆነም ተናግረዋል።

ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለአፍሪካውያንም በራስ አቅም ታላላቅ አህጉራዊ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚቻል መነሳሳትን የፈጠረ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የምትታወቅ ሀገር ናት ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ሕዳሴ ግድብም በፓን አፍሪካኒዝም መርህ ተገንብቶ ብሔራዊ ክብሯ ለመሆን በቅቷል ብለዋል።

በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የታለፉ ውጣ ውረዶችና ጫናዎችም ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ ሀገራቸውን ከሚገጥሙ ፈተናዎች ወደ ድል ማሸጋገር እንደሚችሉ ያረጋገጠ መሆኑን አብራርተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግደብ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ሀይል በማስተሳሰር አጀንዳ 2063 ለማሳካት የሚያግዝ የጋራ ተጠቃሚነት መገለጫ እንደሆነም አስረድተዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬኒያና ታንዛኒያ ጋር የኃይል አቅርቦት የትብብር ሰምምነት እንዳላት ተናግረዋል።

ይህም ግድቡ በቀጣናው የጋራ ልማትን በማረጋገጥ አብሮ የማደግ ራዕይን የሚያሳካ ያደርገዋል ነው ያሉት።

አፍሪካን በንግድና ኢንቨስትመንት በማስተሳሰር አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የሕዳሴ ግድብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 ስኬት የራሷን አስተዋጽኦ በማበርከት ከፍተኛ ጥረት ላይ መሆኗን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.