የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ከተረጂነት ወደ አምራችነት የተሸጋገሩት የምስራቅ ሀረርጌ ዞን አርሶ አደሮች

Apr 10, 2025

IDOPRESS

የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ተራራማ እና ገደላማ መልክዓ ምድር ስለሚበዛበት ለጎርፍና ለከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ተጋላጭ ሆኖ የቆየ ነው።

አካባቢው ለረጅም ጊዜ ተራቁቶ፣ አፈሩ ተሸርሽሮ ለምነቱን በማጣቱ የተነሳም የአካባቢው አርሶ አደሮች ዓመት ጠብቀው ከሚያርሱት መሬት በቂ ምርት ስለማያገኙ ለዓመታት ለችግር ተዳርገው ቆይተዋል።


በዞኑ የጉራዋ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አኒሳ አኒስ ሸሪፍ፥ አካባቢያቸው ተራራማ በመሆኑ ለጎርፍ አደጋና ለአፈር መሸርሸር በመጋለጡ በበቂ ማምረት ይቸገሩ ነበር።

የሚያመርቱበት መሬት ለምነቱን ከማጣቱ ባሻገር ቀያቸውም በክረምት በጎርፍ እየተጥለቀለቀ ለበርካታ ዓመታት ስቃይ ላይ ቆይተዋል።

በዚህም የሚያመርቱት ምርት አነስተኛ በመሆኑ የምግብ ፍጆታን በራስ አቅም ለመሸፈንና ቤተሰባቸውን በበቂ ሁኔታ ለመምራት ሲቸገሩ እንደነበርም አርሶ አደር አኒሳ አኒስ ያስታውሳሉ።


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ተራራማ አካባቢዎች መልማታቸውን ገልጸው፥ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎች ከፍተኛ ምርት እያስገኙ ነው ብለዋል።

የአፈር መሸርሸር በመቀነሱ ምርታማነት ማደጉን ጠቅሰው፥ ለእንስሳትም በቂ መኖ እያገኘን ነው ብለዋል።


በዞኑ የጎሮ ጉቱ ወረዳ ነዋሪዋ አርሶ አደር ኑሪያ መሀመድ ለረጅም ጊዜ ከሴፍቲኔት መርሃ ግብር በሚያገኙት ድጋፍ ሲኖሩ እንደነበር አውስተዋል።

አሁን ላይ ግን በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውንና ይህም ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንዳሸጋገራቸው ጠቅሰዋል።


የምስራቅ ሀረርጌ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኤሊያስ ሸምሰዲን፥ ዞኑ ተራራማ በመሆኑ አርሶ አደሮች የተፋሰስ ልማት ስራን የህልውና ጉዳይ አድርገው እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በ498 ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ ልማት እየተከናወነ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ዘንድሮ ከ211 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።

በአካባቢው ለምርት አመቺ የሆነ የአፈር ለምነት እየተፈጠረ፣ የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር የውሃ አካላት እየጎለበቱ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

በተፋሰስ ልማቱ ከ729 ሺህ በላይ ዜጎች መሳተፋቸውን ገልጸው የተፋሰስ ልማቱ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና በሌሎች ዘርፎችም ምርታማነትን እያሳደገ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ በልማቱ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ መምጣቱንም ነው ያነሱት።

በዞኑ በሴፍቲኔት ድጋፍ ከሚሳተፉ 377 ሺህ በላይ ሰዎች ውስጥ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማቱ አማካኝነት ከ228 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።


ከሰሞኑ በዞኑ ጉብኝት ያደረጉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፥ የምስራቅ ሀረርጌ ዞን የተራቆቱ አካባቢዎችን በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲያገግሙ ማድረጉ ለሌሎች ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።

በዞኑ በርካታ አርሶ አደሮች በምግብ ራሳቸውን በመቻል ከተረጂነት መላቀቃቸውም፤ የቤተሰብ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ሀገራዊ ጉዞ ውጤታማነት ያሳያል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.