ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዝያ 2/2017 (ኢዜአ)፡-በወላይታ ሶዶ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት ከማጉላት ባለፈ በርካታ ዜጎችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት የኮሪደር ልማቱ ከተማን ውብ፣ ፅዱ እና ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
የከተማው ነዋሪ ወጣት ዎጋሶ ጌታ የኮሪደር ልማት ከመካሄዱ በፊት በከተማዋ በርካታ ስፍራዎች ላይ ቆሻሻ በዘፈቀደ ስለሚጣል ለመጥፎ ጠረን በመዳረግ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን አዳጋች አድርጎት እንደነበር አስታውሷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪዎች በማስተባበር እያከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታና ውበት ከማጉላት ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የጎላ አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑን ተናግሯል።
በከተማው ከ40 ዓመት በላይ እንደኖሩ የገለጹት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ከበቡሽ ዳኛቸው በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የነበሩ የከተማዋ መንገዶች ጠባብ እና በነጻነት ለመንቀሳቀስ ምቹ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል።
በከተማው የኮሪደር ልማት በመጀመሩ ይህ ችግር መፈታቱንና የትራፊክ አደጋና መሰል ስጋቶችንም አስወግዶልናል ብለዋል ።
መንገዶቹ ከመስፋታቸው ባለፈ ጽዱና ንጹህ መሆናቸው ለህሊና ዕረፍት የሚሰጥ ነው ያሉት ወይዘሮ ከበቡሽ፣ ህብረተሰቡም በኮሪደር በለማ የእግረኛ መንገድ ላይ በእግር የመጓዝ ባህሉ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ እንዲስፋፋ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
የኮሪደር ልማቱ አረንጓዴ ስፍራና የህዝብ መዝናኛንም እንዲያካትት መደረጉ ነዋሪዎችም ሆነ ወደ ከተማው የሚገቡ እንግዶች ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ እያገዘ ነው ያሉት ደግሞ መምህር ታረቀኝ በቀለ ናቸው።
በልማቱ የእግረኞችና የተሽከርካሪ መንገዶች መለየታቸው የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ተናግረዋል
የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽህፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አስራት ሉንግሶ በበኩላቸው የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩና ተወዳዳሪና ምቹ የሚያደርጉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በከተማው 100 መቶ ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ከሰባት ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል
የኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየርና ከማስዋብ አንጻር ያለውን ፋይዳ ህብረተሰቡ በመረዳቱ ያደረገው ድጋፍና አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም አቶ አስራት ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቱ ከተማዋን ጽዱና ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈ ከ300 ለሚልቁ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩን የገለጹት አቶ አስራት፣ በከተማዋ የኮሪደር ልማቱን በማስፋፋት ከተማን ለማዘመንና ተወዳዳሪ ለማድረግ ጠንክረን እንሠራለን ብለዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025