የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ስኬታማ አፈጻጸም ተመዝግቧል- ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

Apr 14, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2017(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ስኬታማ አፈጻጸም መመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።


በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

የሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ የዘርፎች ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ማጠናከር፣ የኢንቨስትመንት ንግድን ከባቢ ማሳደግ እንዲሁም የመንግስት የመፈጸም አቅምን ማጎልበት ዓላማ አድርጎ ወደ ትግበራ መግባቱን አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በአራቱም ምሶሶዎች የተሻለ ስኬት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ ይህም የስምንት ነጥብ አራት በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስዝገብ የተያዘው እቅድ እንደሚሳካ ያመላከተ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ኢንቨስትመንትና ቁጠባ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ያላቸው ድርሻ መሻሻሉንም ነው የጠቀሱት።

ኢንቨስትመንት ከሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት አኳያ ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 20 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን አንስተዋል።

የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ ላይ የተሻለ አፈጻጻም መመዝገቡን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ የውጭ ብድር ጫና ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ምጣኔ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢኮኖሚ እድገትን ከማሳላጡ ባሻገር ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የእዳ ሽግሽግ ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በሸቀጦችና የአገልግሎት ወጪ ንግድ የተሻለ አፈጻጸም መኖሩንም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

በሪፎርም ስራው በእዳ ውስጥ የነበሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስራ ወደ ትርፋማነት መሸጋገራቸውንም ገልጸዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት መንግስት ምንም ዓይነት ብድር ከብሔራዊ ባንክ አለመውሰዱን ጠቅሰው፤ ይህም የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ትልቅ ፋይዳ ማበርከቱን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል መንግስት የኑሮ ውድነቱ በዜጎች ላይ ጫና እንዳያሳድር ለሴፍትኔት፣ ለመሰረታዊ ፍጆታ፣ ለነዳጅና ሌሎች ስትራቴጂክ ምርቶች የሚያደርገውን ድጎማ አጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል።

ለአብነትም ለአፈር ማዳበሪያ ብቻ 62 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን ነው የተናገሩት ።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በሀገር ውስጥ፣ በውጭ እና በርቀት የስራ እድል ፈጠራ ውጤታማ ስራ መከናወኑንም ሚኒስትሯ ባቀረቡት ሪፖርት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.