የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በሲዳማ ክልል ከ29 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ተዘጋጅቷል

Apr 15, 2025

IDOPRESS

ሀዋሳ፤ሚያዝያ 6/2017 (ኢዜአ) :- በሲዳማ ክልል ከ29 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ መዘጋጀቱን የክልሉ ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን አስታወቀ ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከ32 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን ከ29 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ማዘጋጀት ተችሏል፡፡

በ4 ሺህ 500 ሄክታር ላይ አዲስ ቡናን ለመትከል ከጥር ወር ጀምሮ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች መቆፈራቸውንና በያዝነው ወር ተከላው እንደሚጀመር ጠቅሰዋል፡፡

የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለቡና ተክል አስፈላጊውን እንክብካቤ የማድረግ እንዲሁም ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎችን በመጎንደልና ነቅሎ በአዲስ የመተካት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በጉንደላና ነቅሎ በመተካት ሥራ ባለፈው ዓመት 8 ሺህ ሄክታር ማሳ ማደስ እንደተቻለ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በዚህ ዓመት ደግሞ 11 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ መታደሱን ገልጸዋል፡፡

ቡና ከሚሰጠው ጠቀሜታው አንጻር በልዩ ትኩረት እየለማ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በክልሉ የአለታ ወንዶ ወረዳ አርሶ አደር እንዳሻው ዩሬ ለዘንድሮ 1 ሺህ 500 ችግኝ ለመትከል ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡

አዲስ የሚተክሉት የቡና ችግኝ ዝርያቸው የተሻሻለ መሆኑን ጠቅሰው ከተተከለ በሁለት ዓመት ውስጥ ፍሬ መስጠት እንደሚጀምር አስረድተዋል፡፡

የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር አየለ ቡናራ፤ አምና 1 ሺህ 500 የቡና ችግኝ መትከላቸውን ገልፀው ዘንድሮሞ ከ 1 ሺህ 700 በላይ ችግኞችን ለመትከል የጉድጓድና ችግኝ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ለሚተክሉት የቡና ችግኝ በቂ የሆነ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት እንደሚጠቀሙ የተናገሩት አርሶ አደር አየለ በመካከሉም የጥላ ዛፎችን እንደሚተክሉ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.