የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ36 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ከክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል

Apr 18, 2025

IDOPRESS

ሚዛን አማን፤ሚያዚያ 9/2017 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ36 ሺህ 600 ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ቡና፣ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ።


የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሥራት መኩሪያ፥ በክልሉ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግና የግብይት አቅርቦት ሥራን በማዘመን ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።


በክልሉ በቡና ማሳ ከተሸፈነው ከ582 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ማሳ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ከብክነት በፀዳ መንገድ ለማግኘት ለቡና አምራቹ ሥልጠና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።


ከዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከታቀደው 67 ሺህ 800 ቶን የቡና ምርት ውስጥ ከ36 ሺህ 600 በላይ ቶን ቡና ለማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡


ለማዕከላዊ ገበያ ከቀረበ ቡና ውስጥ 10 ሺህ 700 ቶን የሚሆነው የታጠበ ሲሆን ከ25 ሺህ 900 ቶን በላይ የሚሆነው ያልታጠበ ቡና መሆኑንም አንስተዋል።


የቡና ምርቱን ለማዕከላዊ ገበያ ያቀረቡት በማህበርና በግል የተሰማሩ አልሚዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ አልሚዎቹ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ለማሳደግ እንዲሰሩ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።


በክልሉ ሕገ ወጥ የቡና ንግድ በታቀደው መጠን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንዳይቀርብ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩን ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.