የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢዜአ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ሀገራዊ መግባባትና ገጽታ ግንባታን የሚያጠናክሩ ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል

Apr 18, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ሀገራዊ መግባባትና ገጽታ ግንባታን የሚያጠናክሩ ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል።

ተቋሙ በአጭር ጊዜያት ውስጥ በኢትዮጵያ ከሚገኙ 584 ወረዳዎች ጋር ቀጣይነት ባለው መልኩ መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል ትስስር መፍጠሩም ተገልጿል።

የኢዜአ አመራሮችና ሰራተኞች የተቋሙን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ገምግመዋል።

በዚሁ ወቅት ኢዜአ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥሩና ሀገራዊ ገፅታ የሚገነቡ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን በስፋት ተደራሽ ማድረጉም ተነስቷል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ሠይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአደረጃጀትና አሰራር እንዲሁም ምቹ የሥራ ከባቢን መፍጠር የሚያስችል ተቋማዊ የሪፎርም ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።

ተቋሙ በዲጂታል አማራጮች በተለያዩ ቋንቋዎች የሀገርን ገፅታ የሚገነቡና የአፍሪካን ጉዳዮችን የሚዳስሱ ዘገባዎች ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ብሔራዊ መግባባትንና የሀገር ገፅታን የሚገነቡ የተለያዩ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በስፋት የዘገባ ሽፋን ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ ያካሄደቻቸው ታላላቅ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎችን እንደ ምቹ እድል በመጠቀም ብሄራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ እና የሀገርን በጎ ገፅታ የሚገነባ የዘገባ ሽፋን መስጠቱንም እንዲሁ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ሀገራዊ ምክክር፣ የባህር በር ጥያቄና ሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች በኢዜአ ሰፊ የዘገባ ሽፋን ከተሰጣቸው ጉዳዮች ተጠቃሾች ናቸው።


ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ በውጤታማነት ለማከናወን በአጭር ጊዜያት ውስጥ በኢትዮጵያ ከሚገኙ 584 ወረዳዎች ጋር ቀጣይነት ባለው መልኩ መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል ትስስር መፍጠሩንም ተናግረዋል።

ኢዜአ ከወረዳዎቹ ጋር የተፈጠረውን ትስስር መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ለእውነት ማጣራት ስራ አቅም አድርጎ እንደሚጠቀምም አንስተዋል።

ወቅታዊ ጉዳዮችን በአግባቡ ተረድቶ ሀገራዊ ተልዕኮን ከመወጣት አኳያ ፈፃሚው በቴክኖሎጂና በዕውቀት መታጠቅ እንዳለበትም ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የተናገሩት።

በቀጣይም በተቋሙ የተጀመሩ የአቅም ግንባታ፣ የቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽን ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አብራርተዋል።

የተቋሙ ሰራተኞችም ኢዜአ የጀመራቸውን የሪፎርም ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እንደሚተጉ አረጋግጠዋል።

አትዮጵያ በጀመረችው የለውጥ ጉዞ ልክ ተቋሙ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዲችል በፍጥነትና በጥራት መረጃዎችን ለማድረስ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገር ውስጥ በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛ ቋንቋዎች እንዲሁም ከውጭ ቋንቋዎች ደግሞ በእንግሊዚኛ፣ ፈረንሳይኛ እና አረብኛ ቋንቋዎችን ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና የሀገር ገጽታን መገንባት የሚያስችሉ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.