የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ለማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ትብብር ሊጠናከር ይገባል - ሚኒስትር መላኩ አለበል 

Apr 18, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ ፤ሚያዝያ 9/2017(ኢዜአ)፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ሀገራዊ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።

ውይይቱ በኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የተመራ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሬታ ሰዋሰው እንዲሁም የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በሪፖርቱ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃና በገንዘብ ሚኒስቴር ዘርፍ የታቀዱ ዋና ዋና ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶችና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተካተዋል።


የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት መንግስት በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ መሰረት የታክስ ገቢን በማሳደግ፣ ወጪን በመቆጣጠር፣ ውጤታማ የዕዳ ማሻሻያ ድርድር በማድረግ፣ የውጭ የልማት ትብብርን በማሳደግና ተቋማዊ ሪፎርምን በማጠናከር መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር እያደረገ ይገኛል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።


አሁን ባለው ተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ እንደ ሀገር ተጠናክሮ ለመውጣት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም የወጪ ንግድና ገቢን የሚጨምሩ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አቶ መላኩ አክለውም፣ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ተገቢውን የመንግስት ገቢ በመሰብሰብና ወጪን በመቆጣጠር የሀገር ሃብት ለታለመለት አላማ እንዲውል ከማድረግ አኳያ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚና ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በጋራ በመስራት የተሻለ የስራ ዕድል እና የሀብት መፍጠሪያ ማድረግ እንደሚገባ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.