ጎንደር ፤ ሚያዚያ15/2017(ኢዜአ)፡- በየተመደቡበት መስክ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታን ለመፍጠር ተግተው እንደሚሰሩ በጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች ተናገሩ ።
የከተማ አስተዳደሩ በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ያለመ የውይይት መድረክ ዛሬ አካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊ ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት መንግስት ዘመኑን የዋጀ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለመዘርጋት የጀመራቸውን አዳዲስ የሪፎርም ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
ከሠራተኞቹ መካከል አቶ ዘርፈሸዋ በትሩ ፤ ከተለመደው ኋላ ቀር የአገልግሎት አሰጣጥ መዋቅር የተላቀቀ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት በመዘርጋት ደንበኞች ከሙስናና ብልሹ አሰራር ነጻ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።
እርሳቸውም በተመደቡበት የስራ መስክ ላይ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት በህዝቡ ዘንድ እርካታ ለመፍጠር ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
መልካም ስነ ምግባር የተላበሰ ትጉህና ታታሪ ሲቪል ሰርቫንት በመገንባት ረገድ መንግስት የጀመራቸው የሪፎርም ተግባራት እንዲጠናከር የሚደግፉ መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮ የዝባለም ወረታ ናቸው፡፡
የአገልጋይነት መንፈስ በተላበሰ መንገድ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የአመለካከትና የአስተሳሳብ አንድነት ማምጣት አለብን ብለዋል፡፡
አቶ አብደላ መሃመድ በበኩላቸው፤ የመንግስት ሠራተኛው በዜጎች የአገልግሎት አሰጣጥ ቻርተር የተቀመጠውን የአሰራር ስርዓት ሙሉ በሙሉ በመተግበር ረገድ ጉድለቶች አሉብን ሲሉ ገልጸዋል።
"ህዝብን ማገልገል የመንግስት ሠራተኛው ግንባር ቀደም ተልእኮ ነው" ያለው አቶ አብደላ፤ ዘመኑን የዋጀ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት እውን እንዲሆን የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡
መድረኩ የመንግስት ሠራተኛውን የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶች በሚገባ ያመላከተ በመሆኑ በቀጣይ ጉድለቶቻችን በማረም በየተመደብንበት መስክ የተጣለብንን ሃላፊነት በአግባቡ እንወጣለን ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡
የከተማው አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ፤ በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደሎች ለመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች ምንጭ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደሎችን ለማረም በናሙና በተመረጡ የከተማው የመንግስት ተቋማት ላይ ጥናት መደረጉን ጠቁመው ፤ በጥናቱ መሰረት በቀጣይ የማስተካከያ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የህዝቡን ቅሬታዎች ለመፍታት የሚያግዙ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራር ትግበራ መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025