የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የ5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ በዘርፉ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ያደርጋል- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

May 6, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 26/2017 (ኢዜአ)፡-የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ በዘርፉ ተጨማሪ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የሚያደርግ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ።


የ''አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ ስልጠና ሐምሌ 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ መደረጉ ይታወሳል።


መርሃግብሩ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው።


የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ከመሰረተ ልማትና አስቻይ ስርዓት ከመዘርጋት በተጨማሪ የዲጂታል ክህሎት ያለው ማህበረሰብ አስፈላጊ ነው።


ስልጠናውን የተከታተሉ የመንግስት ሰራተኞች ለስራቸው ውጤታማነት እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው፥ አዳዲስ የስራ እድል መፍጠር የቻሉ እንዳሉም ተናግረዋል።


በተጨማሪም የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ በዘርፉ ተጨማሪ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲመጣ ያደርጋል ብለዋል።


በመርሃግብሩ የሚሰጠው ስልጠና ከዲጂታል ክህሎት በተጨማሪ እውቀትን መሰረት ያደረገና ምክንያታዊ ውሳኔዎችን መስጠት የሚያስችሉ ክህሎቶችን ማግኘት የሚቻልበት እንደሆነም ተናግረዋል።


ስልጠናውን የተከታተሉ ወጣቶች በበኩላቸው ያገኙት ክህሎት ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውና ለስራቸው ተጨማሪ ክህሎትና እውቀት ያስጨበጣቸው መሆኑን ገልፀዋል።


ከሰልጣኞቹ መካከል ወጣት ዲቦራ የኔሰው እንዳለችው፥ ስልጠናው በነፃ የሚሰጥና ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ በመሆኑ ሁሉም እድሉን መጠቀም አለበት ብላለች።


ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ፅዮን ዘለቀ በበኩሏ፥ ስልጠናው ሳቢ በሆነ መልኩ የሚሰጥና ተጨማሪ የስራ እድልን ለማግኘትና ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልፃለች።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.