የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎች የልማት ተግባራት የተመዘገቡ ስኬቶች በራስ አቅም መበልጸግ እንደሚቻል ያረጋግጣሉ

May 7, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎች የልማት ተግባራት የተመዘገቡ ስኬቶች በራስ አቅም መበልጸግ እንደሚቻል የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ።


ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የልማት መርሃ ግብሮቸን በመቅረጽና ህዝብን በማስተባበር የተከናወኑ ተግባራት ለአዳዲስ ሥራዎች የሚያነሳሱ ናቸው።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከስንዴ ምጽዋት ተላቃ ወደ ውጭ መላክ መጀመሯን ሲያበስሩ ባደረጉት ንግግር ታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ የሚጠናቀቁ የማይመስላቸው በርካታ እንደነበሩ ነው የተናገሩት።


በተለይም ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን ትችላለች ከራሷም አልፋ ለሌሎች ትተርፋለች ሲባል እውን የሚሆን ያልመሰላቸው እንደነበሩ አውስተዋል።


በአገሪቷ በህዝብ ቁጥርም ሆነ በተፈጥሮ ሃብት ያላትን እምቅ አቅም አሟጦ መጠቀም ከቻለች ከራሷ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ጥሪት ማፍራት እንደሚቻል የሚያሳዩ መሆናቸውን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ይናገራሉ።


የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግሞ ለዚህ አብነት መሆኑን የሚጠቅሱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስርዓተ-ምህዳር መምህርና ተመራማሪ ቢቂላ ወርቅነህ (ዶ/ር) ናቸው።


ዶክተር ቢቂላ እንደገለጹት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ አሻራ ያረፈበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።


የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ በአንድነት መስራት የመቻላቸው ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።


ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምትችል ትምህርት የተወሰደበት መሆኑንም አንስተዋል።


የአገር አቀፉ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ብሄራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከፍተኛ በጀትና የሰው ሃይል የሚጠይቁ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምትችል በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።


ዶክተር አደፍርስ አረንጓዴ አሻራ እና የስንዴ ልማትን የመሳሰሉ የልማት ተግባራትም ህዝብን በማስተባበር ለዓለም ተምሳሌት የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ያረጋገጡ ተግባራት መሆናቸውንም ተናግረዋል።


ምሁራኑ በቀጣይም የህብረተሰቡን አቅም በማስተባበርና በአግባቡ በመጠቀም ሌሎች የሀገሪቱን ጸጋዎች በማልማት ትልልቅ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደሚቻልም ብዙ ማሳያዎች እንዳሉ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.