የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ጂኦ-ፓርኮችን በኢትዮጵያ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማስጀመሪያ እና ግንዛቤ መፍጠሪያ ወርክሾፕ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

May 7, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦ የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦ-ፓርኮችን በኢትዮጵያ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማስጀመሪያ እና ግንዛቤ መፍጠሪያ ወርክሾፕ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።

ወርክሾፑን አስመልክቶ ሚኒስትሯ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

መንግስት ለቱሪዝም ልማት በሰጠው ትኩረት መጠነ ሰፊ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችንና መሰረተ ልማቶችን በማልማት ዘርፉን የማነቃቃትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን የማጉላት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ይሁን እንጂ አሁንም ካለው እምቅ የቱሪዝም ልማት አኳያ ሰፊ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ወርክሾፑ በጂኦ-ፓርክና በጂኦቱሪዝም ላይ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ በማሳደግና አቅማቸውን በማጠናከር ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የግሎባል ጂኦ-ፓርክስ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር የሚያስችል መነቃቃት ለመፍጠር ያለመ ነው።

ወርክሾፑ "የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦ-ፓርኮች እና ጂኦ-ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

መድረኩ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግና አቅማቸውን ለማጠናከር የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከግንቦት 4 እስከ 7 በሚካሔደው በዚሁ ወርከሾፕ ከኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ እና ዩጋንዳ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

በዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የግሎባል ጂኦ-ፓርክስ ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንዲቻል ሰፊ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።

ዩኔስኮ እስካሁን በርካታ ዓለም አቀፍ ጂኦ-ፖርኮችን ለይቶ ጥበቃ እያደረገ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በአፍሪካ ተመዝግበው የሚገኙ ሁለት ብቻ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም ወርክሾፑ የቀጣናውን የቱሪዝም ሃብት ለመለየትና ያላቸውን ፋይዳ ለማጉላት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያልታወቁ የቱሪዝም ሃብቶችን በመለየት እውቅና ለማሰጠትና እንዲጠበቁ ለማድረግ ምቹ እድልን ይፈጥራል ብለዋል።


የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ሪታ ቢሶናውት በአፍሪካ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ብዙ ጂኦ-ፖርኮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የጂኦ-ፓርኮች መዳረሻዎችን በማልማት ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ ለማስፋት ዩኔስኮ በትኩረተ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወርክሾፑ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚሳተፉ ባለሙያዎች በዘርፉ ለውጥ የሚያመጡ ውይይቶችን ያደርጋሉ ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.