የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የፈጠራ ሥራ ውድድርና አውደ ርዕይ ወጣቶችን በዘርፉ በማነቃቃት ለሀገር የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር እያስቻለ ነው

May 8, 2025

IDOPRESS

ሰቆጣ፤ሚያዚያ 29/2017(ኢዜአ)፦በየዓመቱ የሚካሄደው የፈጠራ ሥራ ውድድርና አውደ ርዕይ የወጣቶችን በዘርፉ በማነቃቃት ለሀገር ልማት የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችንለመፍጠርና ለማሸጋጋር እያስቻለ መሆኑ ተገለጸ።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የተማሪዎችና የመምህራን የፈጠራ ሥራ ውድድርና አውደ ርዕይ ዛሬ በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ በስነ ሥርአቱ ላይ እንደገለጹት በፈጠራ ሥራ ውድድርና አውደርዕዩ ላይ መምህራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

በየዓመቱ በፈጠራ ሥራ እየተካሄደ ያለው ውድድርና አውደርዕይ ወጣቶችን በዘርፉ በመነቃቃት ለሃገር ጭምር የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

ውድድሩ ከዚህም ባለፈ ለቴክኖሎጂ ሽግግርም እያገዘ መሆኑን ነው አቶ ሃይሉ ያስታወቁት።

የተማሪዎችና የመምህራንን የፈጠራ ሥራዎች የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል መጠቀም እንደሚገባ የገለጹት ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪው፣ የተማሪዎችን የፈጠራ ሥራ ማሳደግ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ሚናው የጎላ መሆኑንም ጠቅስዋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ፍትሃለሽ ምህረቴ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የፈጠራ አውደ ርዕዩና ውድድሩ ተማሪዎችና መምህራን እርስ በእርስ ልምዳቸውን ለመለዋወጥ አስችሏቸዋል።

"ይህም ተማሪዎችና መምህራን የጎደላቸውን ከሌሎች በመሙላት የፈጠራ እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ይበልጥ እንዲያጎለብቱ ያግዛቸዋል" ብለዋል።

በውድድሩ 13 ተማሪዎች እና ሦስት መምህራን የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ይዘው መቅረባቸውን የገለጹት ሃላፊዋ፣ ዓላማውም ችግር ፈች የፈጠራ ሥራዎችን ማስፋት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአስተዳደሩ ዝቋላ ወረዳ የሰርካለም ታደሰ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ብርሃኑ ካሳ በውድድሩ ዓይነ ስውራንን የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ፈጥሮ ይዞ መቅረቡን ተናግሯል።

የፈጠረው ቴክኖሎጂ ማየት የተሳናቸው ወገኖች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ለጉዳት የሚዳርግ ነገር ሲያጋጥማቸው በጆሮ ማዳመጫ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁሟል።

መሳሪያው ከወዳደቁና በአካባቢ ከሚገኙ ቁሶች የተሰራ መሆኑን ጠቁሞ፣ በውድድሩ መሳተፉ የፈጠራ ስራውን አጎልብቶ ለመስራት የሚያስችል ሀሳብና ተሞክሮ ማግኘቱን ተናግሯል።

የጭላ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ደበሳው አባይ በበኩላቸው ሥጋ፣ ሽንኩርትና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን መፍጨት የሚችል ማሽን ሰርተው ለውድድር መቅረባቸውን ገልጸዋል።

የፈጠራ ሥራው በሰው ጉልበት እና በኤሌክትሪክ ጭምር የሚሰራ በመሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርገው ጠውሰው፣ ቴክኖሎጂው ሥራዎችን በፍጥናት ስለሚያከናውን ጊዜና ጉልበት ይቆጥባል ብለዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለአንድ ቀን በተካሄደ የተማሪዎችና የመምህራን የፈጠራ ሥራ ውድድርና አውደ ርዕይ አሸናፊ ለሆኑ የፈጠራ ስራዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

በቀጣይ በክልል ደረጃ ለሚካሄድ የፈጠራ ስራ ውድድር ተሳታፊ እንደሚሆኑም ነው የተገለጸው።

በመርሃ ግብሩ ላይ የአስተዳደሩ አመራሮችና የትምህርት ባለሞያዎች መገኘታቸውም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.