የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

አምራች ባለሀብቶችን የመሳብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ቋሚ ኮሚቴው

May 8, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2017(ኢዜአ)፦በኢንዱስትሪ ፓርኮች አምራች ባለሀብቶችን የመሳብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።


በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች 12 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ተኪ ምርት ማምረት መቻሉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል።


በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።


በግምገማው የኮርፖሬሽኑ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከመሰረተ ልማት አቅርቦት እንዲሁም ምርታማነትን ከማሳደግ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።


ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት እንዲሁም የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ማበረታታት ላይም ይበልጥ መሥራት እንደሚገባም ነው የቋሚ ኮሚቴው አባላት አጽንኦት የሰጡት።


የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ የድሬዳዋ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለማስገባት በርካታ የቅደመ ዝግጅት ተግባራት ተከናውነዋል።


በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ 48 ሄክታር መሬት ለነጻ ንግድ ቀጣና ዝግጁ መደረጉን አስታውሰው፥ አስፈላጊውን መሰረተ ልማት በማሟላት ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል።


በዚህም 30 ባለኃብቶች ቦታ ተረክበው ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።


የመቀሌ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የውሃ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አገልግሎት ተሟልቶሎት ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል።


እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ውጭ ከተላከው ምርት 83 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።


ከውጭ የሚገባውን ምርት መተካት ላይም ትልልቅ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 12 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያለው ተኪ ምርት መመረቱንም አብራርተዋል።


የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽናንና ማኔጅመንት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ከማል ኢብራሂም በበኩላቸው፥ የተገነቡ የኢንዱስትሪ ሼዶች በባለኃብቶች የመያዝ ምጣኔ ወደ 87 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል።


ይህም በሥራ ዕድል ፈጠራና ተኪ ምርቶችን ማሳደግ ላይ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ አወንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።


የለማ መሬትን ለባለኃብቶች ከማቅረብ አኳያም ኮርፖሬሽኑ ካለው 423 ሄክታር መሬት ውስጥ 230 ሄክታር መሬቱን በተያዘው ዓመት ለባለኃብቶች ማቅረቡን ተናግረዋል።


በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ(ዶ/ር) ኮርፖሬሽኑ ለአምራቾች ለምርት ግብዓት የሚሆን ጥሬ እቃ ማቅረብ ላይ የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


ባለኃብቶች የመሳብ ሥራው አሁንም ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን ያስገነዘቡት ምክትል ሰብሳቢው፥ ምርታማነትን ማሳደግ ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.