የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ስራዎች የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል

May 8, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2017(ኢዜአ)፦የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ስራዎችን የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቅንጅታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ገለጸ።


ባለሥልጣኑ ከህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጋር በመተባበር የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የትብብርና የቅንጅት ስራዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለስራቸው ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ባለፉት ዓመታት በርካታ የሪፎርም ስራዎች ተከናውነዋል።


በዚህም የፖሊሲና ህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንና የተቋማት አቅም የመገንባት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።


ይህንን ተከትሎ በተለይ ባለፉት የሪፎርም ዓመታት በርካታ ሲቪል ድርጅቶች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡


በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ከስምንት ሺህ በላይ ድርጅቶች ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሲሆን፤ 60 በመቶ የሚሆኑት ባለፉት የሪፎርም ዓመታት የተመዘገቡ መሆናቸወን ገልጸዋል።


እንደ አቶ ፋሲካው ገለጻ፤ የትብብር ስራዎችን በተደራጀ ስርዓትና በዘላቂነት ለማስቀጠል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከሚመለከታቸው ዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር የማቀናጀት ስራ እየተሰራ ነው ።


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የትብብርና የቅንጅት መድረክ መቋቋሙንም አንስተዋል ።


ይህ ትብብር እና ቅንጅት የአገሪቷን ውስን ሀብት አጠቃቀም እንደሚያሻሽል፣የስራ መደራረብን እንደሚቀንስ እንዲሁም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።


ከዚህም በተጨማሪ የፋይናንስ፣የአቅምና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።


የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ስራዎች የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቅንጅታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አቶ ፋሲካው ሞላ አስገንዝበዋል፡፡


የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ በበኩላቸው፥ የተቋሙ ስልጣንና ተግባር በተመለከተ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመፍታት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ መስራት ጉልህ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።


በጥናት፣በትምህርትና ስልጠና ስራዎች ላይም ከድርጅቶቹ ጋር በጋራ ለመስራት ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.