ወልቂጤ፤ ግንቦት 3/2017(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ገንብቶ በማጠናቀቅ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ የም ዞን ከ600 በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የኮሾ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
በዚህን ጊዜ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ኑሪዬ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ በራስ አቅም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም የክልሉን የልማት አቅም ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በግንባታ ላይ ያሉ የመስኖ አውታሮች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የተጀመረውን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞን ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የፕሮጀክት አመራርና አስተዳደርን በመፈተሽ በክልሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተገንብተው እንዲጠናቀቁ በማድረግ አርአያነት ያላቸው ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
ለዚህም የኮሾ የመስኖ ፕሮጀክት በራስ አቅም ልማትን ማፋጠን እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት።
የኮሾ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ዓመቱን ሙሉ ማምረት የሚያስችለው ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ ናቸው።
ግንባታቸው ተጓተው የነበሩ ፕሮጀክቶችን ችግር በመለየት ለውጤት እንዲበቁ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የክልሉ የመስኖ ተቋማት አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ካሳዬ ተክሌ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት እየተገነቡ ካሉ 18 የመስኖ ፕሮጀክቶች ውስጥ ዘጠኙ መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
ዘንድሮ በ87 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ወደ ስራ የገባው የኮሾ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት 150 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው ሲሆን ከ600 በላይ አባወራዎችንም ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሺመልስ እጅጉ የመስኖ ልማት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ መስኖውን በአግባቡ በመያዝና በመጠቀም የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማጠናከር ይሰራል ነው ያሉት።
በዞኑ የሳጃ ደሪ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር እድሌ መርሻ እና አጥናፉ ወልደኢየሱስ በበኩላቸው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ገበያን ለማረጋጋት የመስኖ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቱን በመጠቀም ማሽላ፣ በቆሎ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት መጀመራቸውን ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ከዝናብ ጥገኝነት እንዳላቀቃቸው ተናግረዋል።
ከመስኖ ልማቱ ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ የሚቀርብ ምርት በማምረት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ተግተው እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025