የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተዋናዮች በጂኦፓርኮች እና ጂኦ ቱሪዝም ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ለዘርፉ እድገት ወሳኝ ነው - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ

May 13, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፦ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተዋናዮች በጂኦፓርኮች እና ጂኦ ቱሪዝም ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ለዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለፁ።

ቱሪዝም ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ጋር "የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ለዘላቂ ልማት ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የዩኔስኮ የአፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሸን እና የኢትዮጵያ ላይዘን ቢሮ ኃላፊ ሪታ ቢሶኖውት(ዶ/ር) እንዲሁም የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች፣ በዘርፉ የተሰማሩ የኢትዮጵያውያንና የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ባለሞያዎች ተገኝተዋል።

አውደ ጥናቱ በዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክስ እና ጂኦቱሪዝም ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላትን አቅም ማሳደግ ጨምሮ የዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክ ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያ እና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማስጀመር ያለመ ነው።

በተጨማሪም የጂኦፓርክን ጽንሰ ሃሳብ በአህጉሪቱ ማስተዋወቅ ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው አምስት የኢኮኖሚ አውታሮች አንዱ ቱሪዝም ነው።

ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል ለሀገር እድገት እንዲያበረክት እየተመራ እንዳለ አንስተው፤ ይህም በተሰጠው ትኩረት ልክ ያሉ እድሎችን ለማዳበር እና ለማስተዋወቅ አስተዋጽኦ ፈጥሯል ነው ያሉት።

አዲሱ ረቂቅ የቱሪዝም ፖሊሲ የጂኦቅርስ ቦታዎችን መጠበቅ፣ ጂኦፓርኮችን ማቋቋም እና የጂኦቱሪዝም አስፈላጊነት ላይ ትኩረት የሰጠ ነው ብለዋል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተዋናዮችን በጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ለዘርፉ ዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዛሬው መድረክም የዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክስ እና ጂኦቱሪዝም ጽንሰ ሀሳብን ለማስተዋወቅ ያግዛል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.