የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ዩኔስኮ በኢትዮጵያ ለቱሪዝም ልማት የሚውሉ ከ10 እስከ 20 የሚሆኑ ጥብቅ ስፍራዎችን መለየቱን ገለጸ

May 15, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ ለቱሪዝም ልማት የሚውሉ ከ10 እስከ 20 የሚሆኑ ጥብቅ ስፍራዎችን መለየቱን አስታውቋል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ጋር በመሆን "የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ለዘላቂ ልማት ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

አውደ ጥናቱ የቱሪዝም ሀብቶች እና አቅሞችን መጠቀም ላይ ያተኮረ ነው።

የዩኔስኮ ከፍተኛ የፕሮግራም ስራ አስፈጻሚ ኦዝሌም አዲያማን ኢትዮጵያ ለልዩ መልክዐ ምድር ቱሪዝም (ጂኦ ቱሪዝም) የሚሆኑ እምቅ ሀገር በቀል ሀብቶች እንዳሏት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የቱሪዝም ልማት እና የጥብቅ ስፍራዎች ከፍተኛ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችላት ሀገራዊ እና አህጉራዊ የቱሪዝም አቅም እንዳላት አመልክተዋል።

በዩኔስኮ ጥብቅ ስፍራ ተብለው የተለዩ ስፍራዎች የምድርን ተፈጥሯዊ ቅርሶች ለመጠበቅ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

መልክዐ ምድራዊ የቱሪዝም ሀብቶች በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ መመዘኛ የወጣላቸው ቢሆንም ሀገራት በራሳቸው መንገድ የባህል እና የተፈጥሮ ስፍራዎችን መሰየም እንደሚችሉም ነው የጠቆሙት።

ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ ሁኔታ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ናት ያሉት የፕሮግራም ስራ አስፈጻሚዋ በተፈጥሮ እና በባህል የካበተ ሀብት ባለቤት እንደሆነችም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የአፈጣጠር መገኛ እና ዓለም እንዴት እንደተፈጠረ ማሳያ ናት፤ ከምድር ስሪት አንጻር የመሬት አፈጣጠር ታሪክ የያዘች ሀገርም ናት ብለዋል ኦዝሌም አዲያማን።

ዩኔስኮ የዋሻዎች ስርዓትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ለቱሪዝም ልማት የሚውሉ ከ10 እስከ 20 የሚሆኑ ጥብቅ ስፍራዎችን መለየቱን ገልጸው ይህም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን የመልማት አቅም የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ድርጅቱ ኢትዮጵያ በብሄራዊ የፖሊሲ ማዕቀፏ ጥብቅ ስፍራዎች ለማልማት እና የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እያከናወነች ያለውን ስራ ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.