የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ ድጋፍና ዕውቅና አግኝቷል - የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ

May 16, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተገኙ ባሉ ውጤቶች ዓለም አቀፍ ድጋፍና ዕውቅና መገኘቱን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ በፋይናንስ ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎችና የተገኙ ውጤቶችን በፎረሙ ላይ አቅርበዋል።

በፋይናንስ ዘርፍ የተደረገው ማሻሻያ መነሻ፣ የማሻሻያውን ይዘት፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ የዘርፉን እቅድ በዝርዝር አቅርበዋል።

የውጭና የሀገር ውሰጥ የብድር ጫና መጨመር፣ የዋጋ ግሽበትና ሌሎች ያስከተሉት የማክሮ ኢኮኖሚ አለመጣጣም ለማሻሻያው መነሻ እንደሆኑ አስታውሰዋል።


በማሻሻያው ትኩረት ከተደረገባቸው ነጥቦች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ዘመናዊ ማዕከላዊ ባንክ የሚያደርጉ አሰራሮችን መዘርጋት፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር፣ የፋይናንስ መረጋጋትን ማምጣት ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

በማሻሻያው የፋይናንስ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመደገፍ አዳዲስ አሰራሮችና ገበያዎችን መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።

የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን መደረጉን ጠቅሰው፤ ለግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ፈቃድ በመስጠት ወደ ስራ መግባታቸውንም አብራርተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የተመዘገቡ ውጤቶችን የዘረዘሩት የባንኩ ገዥ፤ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት መጨመር፣ የዋጋ ግሽበት መቀነስ፣ በፋይናንስ ዘርፉ መረጋጋት መታየቱ ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል።


የባንክ ዘርፉን ለዓለም አቀፍ ተቋማት ክፍት ማድረግ፣ በባንኮች መካከል ያለው ግብይት መጨመር እና መንግስት ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደውን ብድር ዜሮ ማድረስ መቻሉንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የተረጋጋ ምጣኔ ሃብት ለመፍጠር በወሰደችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና እየተገኙ ባሉ ውጤቶች ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ድጋፍና እውቅና እያገኘች መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም የዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣ ከቻይናና ሌሎች ሀገራት የእዳ መክፈያ እፎይታ ጊዜና የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲጂታል ፋይናንስ ክፍያ፣ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ መጠን መጨመር፣ የፋይናንስ አካታችነትና ሌሎች ቀጣይ በፋይናንስ ዘርፉ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.