አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው መንግስት የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም መንግሥት ለሰላም ትኩረት በመስጠት ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዞ በመቀበል ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር የሰላም ጥሪውን በማይቀበሉ ቡድኖች ላይ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ውጤታማ የህግ ማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎች ባከናወናቸው ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
መንግስት በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የማህበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በወሰደው እርምጃ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ከ21 ሚሊየን በላይ ዜጎችን በማሳተፍ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በመስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎችም ዘርፎች እመርታዊ ለውጦች መታየታቸውን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በበጋ ስንዴ ልማት 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ66 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 235 ሺህ ሄክታር በኩታ ገጠም መልማቱንም ተናግረዋል።
መንግስት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በምግብ እህል ራስን ለመቻል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ምርጥ ዘር ስርጭትን ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ መሆን ገልጸዋል።
በዚህም በ2017/18 የምርት ዘመን ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር መመደቡን አስታወሰው፣ 84 ቢሊየን ብር ድጎማ አድርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪው ለዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሥነ ምህዳር በመዘርጋት ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የጎላ አበርክቶ እንዳለውም አንስተዋል።
ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውሰዋል፡፡
ንቅናቄው በኮቪድ ወረርሽኝና ሌሎች ዓለም አቀፍና ተጽዕኖዎች ምክንያት ተዳክሞ የቆየውን የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ46 በመቶ ወደ 62 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት 10 ነጥብ 34 ቢሊየን ዶላር ግምት ያለው የውጭ ምርት መተካት መቻሉንም ተናግረዋል።
መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን አንድ የኢኮኖሚ የትኩረት መስክ በማድረግ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማደስና አዳዲስ መገንባት መቻሉንም አንስተዋል፡፡
የላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲል ግንብ፣ የጀጎል ግንብ፣ የጅማ አባ ጅፋር፣ አክሱምና ሌሎች ቅርሶችን በማደስ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለትውልድ መርሀ ግብሮች በርካታ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች መገንባታቸውንና እየተገነቡ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ለማስፋት አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል፣ ሳይንስ ሙዚያም እና ሌሎች ማዕከላትን በመገንባት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን እያስተናገደች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ባለፉት አስር ወራት ብቻ 84 ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን በብቃት በማከናወን ከ30ሺህ በላይ የውጭና ከ171 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ማሳተፍ ተችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተያዘው ግንቦት ወር ብቻ የተካሄዱትን ጨምሮ ስምንት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን እንደምታስተናግድ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን/ETEX 2025፣ አይ ዲ 4 አፍሪካ ዓመታዊ ጉባኤ እና 20ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት አህጉራዊ ኮንፍረንስ በርካታ ተሳታፊዎች ከሚታደሙባቸው ሁነቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025