የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በምስራቅ ቦረና ዞን በበጀት ዓመቱ 46 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ

May 16, 2025

IDOPRESS

ነገሌ ቦረና፤ግንቦት 8/2017(ኢዜአ)፦በምስራቅ ቦረና ዞን በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት 46 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን የዞኑ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡


የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ ተወካይ አቶ ዳግም ማንያዘዋል እንዳሉት፥ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ወራት በዞኑ አምስት ወረዳዎች ከ124 ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር ተደራሽ መንገዶች ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡


የመንገድ ግንባታዎቹም በዞኑ አሬሮ፣ ጉሚ ኤልደሎ፣ መዳ ወላቡ፣ ዋጭላና ምዕራብ ወላቡ ወረዳዎች መሆኑን ገልጸው፥ እስካሁን በጉሚ ኤልደሎ 20 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በአሬሮ የ26 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ መጠናቀቁን ተናግረዋል።


ግንባታቸው ለተጠናቀቀው የመንገድ ፕሮጀክቶች ከ48 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉንም አቶ ዳግም አስታውቀዋል፡፡


የገጠር መንገዶቹ ቀበሌን ከቀበሌ፤ ወረዳን ከቀበሌ እና ተጎራባች ወረዳዎችንና ዞኖችን እርስ በእርስ የሚያገናኙ መሆናቸውንም አክለዋል።


አጠቃላይ በግንባታ ላይ የሚገኙ መንገዶች ግንባታ ማስፈጸሚያ የሚውል ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከ239 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን ገልጸው፥ በሂደት ላይ ያሉ ግንባታዎችን ፈጥኖ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


በዞኑ ምዕራብ ወላቡ ወረዳ የኦበርሶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተፈሪ ወንድሙ፤ በአካባቢያቸው ያለው መንገድ ምቹ ባለመሆኑ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማጓጓዝም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበረ ተናግረዋል።


በአካባቢው የገጠር መንገድ ግንባታው በመጠናቀቁ የማርና የቡና ምርታቸውን በቀላሉ በመኪና አጓጉዘው ለገበያ ለማቅረብ እንደሚያግዛቸው ተስፋ አድርገዋል።


መንገዱ ወረዳችንን ከሌሎች ወረዳዎችና ከነገሌ ቦረና ዋና መንገድ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ችግራችንን ያቃልላል ያሉት ነዋሪው የመንገዱ ግንባታ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ድጋፍና ትብብራችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡


የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ ጎሳዬ በቀለ፤ ' የክልሉ መንግስት የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የገባውን ቃል በተግባር እየፈጸመ ነው ብለዋል፡፡


በመንገድ መሰረተ ልማት ረገድ በአካባቢያቸው አበረታች ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎችም እንዲጠናከሩላቸው ጠይቀዋል።


#Ethiopian_News_Agency


#ኢዜአ


#ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.