የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኤክስፖው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማስተዋወቅና ትስስሮችን ለመፍጠር አስችሎናል -በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ የፈጠራ ስራቸውን ያቀረቡ

May 21, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ግንቦት 12/2017(ኢዜአ)፦ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 የቴክኖሎጂ ውጤቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ትስስሮችን ለመፍጠር እንዳስቻላቸው የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ የፈጠራ ስራ አቅራቢዎች ተናገሩ፡፡


በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ለሶስት ቀናት በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 በኢትዮጵያ መካሄዱ ይታወቃል፡፡


ኤክስፖው 2025 በዲጂታላይዜሽንና በቴክኖሎጂ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለዓለም ማስተዋወቅና በርካታ ትስስር መፍጠሩም ተጠቁሟል።


በኤክስፖው በርካታ የሀገር ውስጥ፣ የውጭ ተቋማትና ግለሰቦች የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡


በዚሁ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራ አቅራቢዎች እንዳሉት፤ለአገር ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ልማት ስራዎች ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡


የኦሚሽቱ ጆይ ቴክ ቴክኖሎጂ መስራች መርዕድ ጉግሳ በኤክስፖው በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራን ማቅረባቸውን አንስተዋል፡፡


ቴክኖሎጂው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀምና አፈርን በመመርመር ለየትኛው ዓይነት ሰብል ዝርያ እንደሚስማማ የሚለይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ይህም ምርታና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችም ሙከራ ተደርጎ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


የሚድራፍ ቴክኖሎጂ መስራችና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ራሔል ዘመነ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሎችን እና ክሊኒኮችን ከፋርማሲዎች ጋር የሚያስተሳስር የፈጠራ ስራ በኤክስፖው መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡


በዚህም ያቀረቡት ፈጠራ በዲጂታል (የኢ-መድኃኒት) ማዘዣ እና የዕቃ ዝርዝር አስተዳደር ስርዓቶችን የሚያዘምን መሆኑን ጠቅሰው፤ ፋርማሲዎች ያላቸውን የመድሃኒት ዓይነቶችና ብዛት የሚቆጣጠሩበት አሰራር ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡


በሌላ መልኩም የታካሚዎችን የመድሃኒት ማዘዣዎች መከታተልና የህክምና ታሪካቸውን መመልከት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡


የዩቶጵያ ቴክኖሎጂ የማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ እምሻው ታፈሰ የአረንጓዴ ኢነርጂን ለማስፋፋት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡


በዚህም በአውቶሞቲቭና ግሪን ፈንድ እንዲሁም ፋይናንስን ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያስተሳስሩ ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡


ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማስተዋወቅ ብሎም ትስስሮችን መፍጠር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።


ኤክስፖው ከሀገር ውስጥና ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው የገለጹት የፈጠራ ስራ አቅራቢዎቹ፥ ከፖሊሲ አውጪዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት እንዲፈጥሩም እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡


በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 በዲጂታላይዜሽን እና በቴክኖሎጂ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለዓለም ማስተዋወቅና በርካታ ትስስር መፍጠር ያስቻለ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.