አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ዘላቂና የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት አካታችና ፍትሐዊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ የዓለም የሥራ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጊልበርት ሆንግቦ ገለጹ፡፡
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሰረተ የባለሙያዎች አህጉራዊ ስብሰባ "የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች" በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በመርሀ ግብሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ታድመዋል፡፡
የዓለም የሥራ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጊልበርት ሆንግቦ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ወቅታዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነትን በማዘጋጀቱ ምሥጋና ይገባዋል፡፡
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት ስብሰባ አፍሪካውያን ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር ቃል የሚገቡበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ውጤታማ እና ዘላቂ የሥራ እድል በቂ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዓለም የሥራ ድርጅት ዘላቂ የሥራ ዕድል መፍጠር አይበገሬነትን ለመገንባት መሰረት መጣል ነው ብሎ ያምናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር ሥራ ብቻ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ በሥራ ላይም መብታቸው መከበር አለበት ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ችግሮች ቢኖሩም የለውጥ ሂደቶች እንዳሉ ገልጸው፤ የማህበራዊ ጥበቃና ፍትሐዊነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
የዓለም የሥራ ድርጅት በተጠናከረ የሥራ መሰረተ ልማት ፕሮግራም አማካኝነት ማህበረሰባዊ ሽግግር እንዲፈጠር ድጋፍ ያደርጋለ ብለዋል፡፡
በመሆኑም በአፍሪካ ለአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት የወጣቶችን ሥራ ፈጠራ ለማበረታታት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠዋል፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራና ስራ ስምሪት ለአካታችና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህ መሰረት መሆናቸውን ይገነዘባል ነው ያሉት።
የሥራ እድል ፈጠራን፣ ድህነት ቅነሳንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሀሳቦችን በማፍለቅ የጋራ አንድነትና ቁርጠኝነት የምናሳይበት ስብሰባ ይሆናልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር በቅርበት እንደምትሰራ ገልጸው፤ መንግስት ለሥራ ፈጠራ፣ ለዘላቂ ልማት፣ የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተለይ በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ከስራ እድል ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርን፣ የኮሪደር ልማትና መሰለ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመከታተል ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማትና በሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች በመሆኑ ተሳታፊዎች ልምድ የሚቀስሙበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የሌበር፣ ኢምፕሎይመንት እና ማይግሬሽን ሃላፊ ሳቤሎ ምቦካዚ በበኩላቸው የአጀንዳ 2063 ግብን ለማሳካት የሥራ ፈጠራን የሚያበረታታ ሂደት መከተል ይገባል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ በማህበረሰቡ ዘንድ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት አካታችና ሁሉን አቀፍ የልማት መንገድ በዘላቂነት መከተል እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
20ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት አህጉራዊ ስብሰባ የአፍሪካን መፃኢ ጊዜ የሚወስን ውይይት የሚደረግበት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም በአፍሪካ አካታች የስራ ዕድል በመፍጠር የአህጉሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ቁርጠንኝነታችንን በድጋሚ የምናረጋግጥበት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025