የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በኮሪደር ልማት ውብና ለኑሮ ምቹ ከተማን እውን የማድረግ ጥረትን እያገዝን ነው-የሸገር ከተማ ነዋሪዎች

May 30, 2025

IDOPRESS

ሸገር፤ግንቦት 21/2017(ኢዜአ)፦በኮሪደር ልማቱ ውብና ለኑሮ ምቹ የሆኑ ከተሞችን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እያገዙ መሆኑን የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።


ኢዜአ በሸገር ከተማ አስተዳደር በቡራዩ ክፍለ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ በመቃኘት ነዋሪዎችንም አነጋግሯል።


ነዋሪዎቹ እንዳሉት የኮሪደር ልማት ስራው ውብ እና ለኑሮ ምቹ ከተማ የመገንባት ጥረት በመሆኑ በስራ ሂደቱም ከመንግስት ጎን በመቆም የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ ነው።


ከነዋሪዎቹ መካከል የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ቶሊ ኤግዱ፤ በአካባቢያቸው እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት በገንዘብም በጉልበትም እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል።


በግላቸው ከመንግስት ጎን በመቆም በራሳቸው ወጪና ጉልበት ቤታቸው በር ላይ የሚያልፍ 100 ሜትር ርዝመት ያለው የእግረኛ መንገድ መስራታቸውን ገልጸዋል።


የኮሪደር ልማት ስራው ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ በአቅማቸው ካደረጉት ድጋፍ ባሻገር የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር ሁሉም አሻራውን እንዲያሳርፍ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።


ሌላው የክፍለ ከተማው ነዋሪ ወጣት ብርሃኑ ቀነኒ፣ የኮሪደር ልማት በአካባቢያቸው እንዲከናወን በጉጉት ሲጠብቁ እንደነበረ ገልጾ፥ ስራው ሲጀመርም የራሱን ቤት በራሱ ተነሳሽነት በማፍረስ ለስራው ስኬት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግሯል።


አሁን ላይ የኮሪደር ልማቱ በፍጥነትና በጥራት እየተሰራ ሲሆን በልማቱ ላይ ከመሳተፍም ባሻገር ስራው ሲጠናቀቅም ለትውልድ እንዲተላለፍ እንክብካቤ እና ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባም አስረድቷል።


ወይዘሮ በላይነሽ ሰለሞንም እንዲሁ ከተማቸው ውብና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፥ በኮሪደር ልማቱ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።


በአካባቢያችን በቅርብ ጊዜ ግንባታው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ስለሆነ እኛም የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።


ልማቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከመንግስት ጎን በመቆም በጉልበትም ሆነ በገንዘብ ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።


በሸገር ከተማ አስተዳደር የቡራዩ ክፍለ ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሽብሩ ዓለሙ፣ በከተማው የኮሪደር ልማት ስራ በቅርብ ጊዜ የተጀመረ ሲሆን የተሟላ ግብዓትና የሰው ኃይል ተሟልቶ በፍጥነትና በጥራት እየተካሄደ ይገኛል።


በክፍለ ከተማው 21 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለማከናወን መታቀዱን ገልጸው፥በበጀት አመቱ 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።


ህብረተሰቡን በማስተባበር ውብ፣ሳቢና ለኑሮ ምቹ ከተማን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ጠቅሰዋል።


ነዋሪው እስካሁን በጉልበቱ፣በእውቀቱ፣በሀሳቡና በገንዘቡ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.