የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በሆሳዕና ከተማ 24 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ስራ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው-ከንቲባ ዳዊት ጡምደዶ

May 30, 2025

IDOPRESS

ሆሳዕና፤ግንቦት 21/2017 (ኢዜአ)፦በሆሳዕና ከተማ የመጀመሪያ ምዕራፍ 24 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ስራን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ ገለጹ፡፡


አቶ ዳዊት ጡምደዶ ለኢዜአ እንደገለፁት፥የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ከተሰጡ የልማት ስራዎች አንዱ የኮሪደር ልማት ስራ ነው፡፡


በከተማው በጥቅሉ 35 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አንስተው፥ ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ምዕራፍ የ24 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


አሁን ላይ የአፈር ሙሌትን ጨምሮ አብዛኛው ስራ ተጠናቆ ቴራዞ የማንጠፍ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ እስከሚቀጥለው ሰኔ ወር አጋማሽ ድረስ ባሉት ጊዜያት በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት እንዲገባ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡


በከተማው የጀሎ ናረሞ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ብዙአየሁ መሀመድ በከተማው እየተሰራ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ በፅዳት አጠባበቅና በእግረኛ መንገድ አጠቃቀም ዙሪያ የነበሩ ውስንነቶችን እየቀረፈ ስለመምጣቱም ጠቁመዋል፡፡


እንዲሁም ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለእንግዶች ምቹ ከማድረግ አኳያ እየተሰራ ያለው ስራ ጥሩ በመሆኑ ለልማቱ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል፡፡


በአስተዳደሩ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ከተሞችን ውብና ፅዱ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማምጣቱን የገለፁት ደግሞ በከተማው ሄጦ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አሰፋ ላዕዋሞ ናቸው።


ቀደም ሲል የከተማዋ መንገዶች ጠባብ በመሆናቸው ለትራፊክ አደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን የኮሪደር ልማቱ እንደሚቀርፈው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.