ወልቂጤ፤ ግንቦት 25/2017(ኢዜአ)፦ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሥራ ፈጣሪ የሚሆኑበትን እቅም ከማጎልበት ባሻገር ከቀጣሪ ተቋማት ጋር የሚያገናኙ መድረኮችን እያመቻቸ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው የ2017 ተመራቂ ተማሪዎችን ከቀጣሪ ተቋማት ጋር የሚገናኙበት የሥራና የሙያ አውደ ርዕይ ዛሬ ተከፍቷል።
የወልቁጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ተማራዎችን በእውቀትና በስነ ምግባር ብቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
በጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም አክለዋል።
ለዚህም አምራች ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርግ፣ ምርታማነት የሚያሻሽሉና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አሰራር የሚያዘምኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ተማሪዎች ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ከማድረግ ባለፈ በቀጣሪ ድርጅቶች ተመራጭ እንዲሆኑ የሥራና የሙያ አውደ ርዕይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደሚያዘጋጅም ተናግረዋል።
አውደ ርዕዩ ሰልጣኞች ብቃታቸውን የሚፈትሹበት፣ ከቀጣሪዎች ጋር የሚገናኙበትና የሥራ ዕድል የሚያገኙበት መሆኑንም አስረድተዋል።
ምሩቃን በቀጣይ የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር እንዲችሉ ከሥራ ፈጣሪዎች ልምድ እንዲያገኙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፣ ከቀጣሪ ድርጅቶች ፍላጎት በመነሳት በየትምህርት መስኩ የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አሰልጥኖ የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች በእውቀት፣ በክሎትና በአመለካከት ለማጎልበት የሚሰራውን ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን የሰው ሀይል ከማፍራት ጎን ለጎን ተመራቂዎች ተመራጭ እና ተፈላጊ እንዲሆኑ ከቀጣሪዎች ጋር ማገናኘት የሚያስችል አውደ ርዕይ ማዘጋጀቱ መልካም መሆኑንም ጠቁመዋል።
የበላይነህ ክንዴ ቢዝነስ ግሩፕ የእርሻ ዘርፍ ሀላፊ ቀረብህ መኮንን ድርጅታቸው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ምሩቃንን እንደሚፈልግ ገልጸው፣ በቴክኖሎጂና በተግባቦት ክህሎት ዳብረው የሚወጡ ባለሙያዎች ተፈላጊነታቸው የላቀ ነው ብለዋል።
በግብርና፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በሌሎችም ዘርፎች በተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች በድርጅቱ የተግባር ትምህርት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአውደ ርዕዩ ላይ ሲካፈሉ ከነበሩ የዩኒቨርሲቲው ተማራቂ ተማሪዎች መካከል ራሔል ተፈሪ በሥራ አመራር ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ውጤት ለመመረቅ መዘጋጀቷን ገልጻ፣ አውደ ርዕዩ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ስለሚያገናኝ በቀጣይ የሥራ ዕድል ለማግኘት መልካም መሆኑን ገልጻለች።
ሰላሙ አብርሃም የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመራቂ ተማሪ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲው በስራ ዕድል ፈጠራ ስልጠና በማግኘቱ በቀጣይ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን ተናግሯል።
በአውደ ርዕዩ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ሥራ ፈጥረው ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች አርአያ የሆኑ ወጣቶች ልምዳቸውን አካፍለዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025