አዲስ አበባ፤ግንቦት 25/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ለውጭ ኢንቨስትመንቶች ምቹ እድል መፍጠሯን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የኢትዮ- ቤልጅየም የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፣የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ፣የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣በኢትዮጵያ የቤልጅየም አምባሳደር አኔሊስ ቨርስቲሼል (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት አመራሮችና የቤልጅየም ኩባንያዎች የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየሰራች ነው።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ትልቁን እና በዚህ ወቅት በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
መንግስት አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ የግሉ ሴክተር ተሳትፎ እንዲጎለብት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውጭ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግም ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ወደሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በቀላሉ መድረስ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጭ ኢንቨስትመንቶች ምቹ እድል መፍጠሯንም አንስተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሐመድ ሀሰን በበኩላቸው፥ የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ በርካታ የኢንቨስትመንት ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ቤልጂየም ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት የጋራ ራዕይ እንዳላቸውና መድረኩ እነዚህን ራዕዮች ወደመሬት ለማውረድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፤ የቤልጅየም ኩባንያዎች መምጣት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያሉትን በርካታ የኢንቨስትመንት እድሎች ለመገንዘብ ትክክለኛውን ሀገር ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ጊዜ መምረጣቸውንም አንስተዋል።
የሀገራቱ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት በአስደናቂ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸው፤ በአማካይ በየዓመቱ የ12 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል።
የቤልጂየም ኩባንያዎች እንደ ማኑፋክቸሪንግ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ እና መሠረተ ልማት ባሉ ዘርፎች ላይ በንቃት መሰማራታቸውንም ተናገረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ፈራሚ እና የኮሜሳ አባል መሆኗና ወደ ንግዱ በቀላሉ ለመግባት የሚያበረታቱ ዘላቂ፣እና ንፁህ የኢነርጂ ሃብቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
በኢንቨስትመንት ሕጎች እና ደንቦች ላይ ወሳኝ ማሻሻያዎችን ጨምሮ የተረጋጋ እና ሊገመት የሚችል የኢንቨስትመንት ምህዳር መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል።
እንደ ፋይናንስ፣ቴሌኮሙኒኬሽን ቀደም ሲል ለሀገር ውስጥ የቢዝነስ ተዋንያኖች ብቻ የተቀመጡ ወሳኝ ቦታዎች መከፈታቸውን ገልጸው፤ በገበያ ላይ የተመሰረተ የምንዛሪ ተመን በማድረግ በውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች መቀረፋቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ቤልጅየም ከመቶ አመት በላይ ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የቤልጅየም አምባሳደር አኔሊስ ቨርስቲሼል (ዶ/ር) ናቸው።
ኢትዮጵያ ለቤልጂየም እና ለአፍሪካ ቁልፍ ገበያ ሆና መቆየቷን ጠቅሰው፤ተከታታይነት ባለው ውይይትና ትብብር ንግድን የማዳበር ተግባር እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የወሰደቻቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሚደነቁ እና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደሯ፤ የቤልጅየም ኩባንያዎች በተለያዩ መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
አምባሳደሯ አክለውም፥ የሀገራቱ ግንኙነት የተመሰረተበትን 120 አመት ለማክበርም ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025