የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ለሀላባ - አንጋጫ - ዋቶ እና ደምቦያ - ዱራሜ መገንጠያ መንገድ ግንባታ ማነቆዎችን በቅንጅት መፍታት ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው

Jun 3, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 25/2017(ኢዜአ)፦ ለሀላባ - አንጋጫ - ዋቶ እና ደምቦያ - ዱራሜ መገንጠያ ፕሮጀክት ግንባታ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅትና በፍጥነት በመፍታት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ መመለስ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች እና የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ከኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር በሀላባ - አንጋጫ - ዋቶ እና ደምቦያ - ዱራሜ መገንጠያ መንግድ ፕሮጀክት አፈጻጸምን በተመለከተ ውይይት አካሂደዋል።

በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አበበልኝ መኩሪያ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በተመለከተ ገለጻ አቅርበዋል።

ፕሮጀክቱ የሚሸፍነው 65 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ሲሆን የወሰን ማስከበር ስራ የተጠናቀቀው ግን 37 ኪሎ ሜትር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ያለው አፈጻጸም 23 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑን ገልጸው፤ የፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ጊዜ መራዘሙን አንስተዋል።

ከንብረት ማስነሳትና ወሰን ማስከበር፣ የግንባታ መሳሪያዎች፣ የግብዓቶች አለመሟላት፣ የፕሮጀክት ስጋት አስተዳደር፣ የክፍያ መዘግየትና ሌሎች ችግሮች ለፕሮጀክቱ መዘግየት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓትና የግብዓት አቅርቦት ማሻሻል፣ አማራጭ መንገዶችን መፈለግና ሌሎች የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በተለይም ከአምስት ወራት በፊት በሰጠው አቅጣጫ ለውጥ የተገኘ መሆኑን ገልጸው ድጋፉና ክትትሉ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በውይይቱ የተገኙት የሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላትም ለፕሮጀክቱ ግንባታ መዘግየት ምክንያት የሆኑ ዋና ዋና ችግሮችን ለመፍታት የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።


ተቋማቱ በጋራ በመስራት መንግስትን ከኪሳራ ማዳንና የህብረተሰቡንም ጥያቄ እንዲመልሱ ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እንደ አማካሪ ተቋም ችግሮችን በማሳየት፣ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን በማጠናከር ሚናውን እንዲወጣም አሳስበዋል።

የካሳ ክፍያ፣ የወሰን ማስከበርና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ህብረተሰቡን በማወያየት ለችግሮቹ መፈታት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የመንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር መልካ በቀለ የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የግንባታ መሳሪያዎችን፣ ግብዓቶች ከማሟላትና ከወሰን ማስከበር ነጻ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ግንባታውን ከማከናወን አንጻር ያሉ ክፍተቶችን እንፈታለን ብለዋል።

ከወሰን ማስከበር ስራዎችና ከክፍያ ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታትም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ያለውን ስራ ውጤታማ ለማድረግ የበለጠ ተቀራርቦ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ በእምነት ጋሻው በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በባለቤትነትና በቅንጅት መስራት አለብን ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ዕቅድ፣ ፕሮጀክትና ፕሮግራም ዝግጅት ቢሮ ኃላፊ አብይ ጸጋዬ ለፕሮጀክቱ መዘግየት አንዱ ችግር የቅንጅት ክፍተት በመሆኑ ሀላፊነቱን ወስደን ለመፍትሄው እንሰራለን ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መለስ መና በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ያጋጠሙ ማነቆዎችን ለመፍታት በቅንጅት መስራት፣ የሰው ሀይልና ግብዓቶችን ማሟላትና ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ከክረምት ወቅቱ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ በማስወገድ የህብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

ከክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ህግና መመሪያዎችን በጠበቀ መልኩ ባለድርሻ አካላት በተሻለ ትብብር እንዲሰሩም አሳስበዋል።

የሀላባ - አንጋጫ - ዋቶ እና ደምቦያ - ዱራሜ መገንጠያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በጥር 2013 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረ ሲሆን በ3 ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ሲሰራ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.