አዲስ አበባ፤ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የባለ ብዝሃ ዘርፎችን መሰረት በማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ልማት ላይ ተጨባጭ ውጤቶች እያስገኙ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያን ብልጽግና በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ጥገኛ በማድረግ ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸዋል።
መንግስት ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከነጠላ ወደ ብዝሃ ዘርፍ ሽግግር በማድረግ ልማትን ለማረጋገጥ እና ኢኮኖሚውን ለመለወጥ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና የኢንፎሜሽንና ኮሙኒኬሽንስ ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ዋንኛ የልማት ምሰሶዎች ተደርገው መለየታቸውን አመልክተዋል።
በተለዩት መስኮች ኢትዮጵያ በርካታ አቅሞች እንዳሏት ጠቅሰው ዘርፎቹ እርስ በእርሳቸው የሚመጋገብ ጠቀሜታ እንዳላቸው አንስተዋል።
በዚህም በግብርና ምርታማነት፣ በኢንዱስትሪ እድገት፣ በቱሪዝም ልማት፣ በማዕድን የወጪ ንግድ እና በቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ውጤቶች መገኘታቸውን ነው ያነሱት።
የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማሳያነት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተከናወኑ ስራዎች ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገቡን አመልክተዋል።
ከንቅናቄው በፊት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 48 በመቶ ገደማ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ይህ አሃዝ 65 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል።
ከለውጡ በፊት የነበሩ ሶስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሁን ላይ ወደ 13 ከፍ ማለታቸውንና በፓርኮቹ ያሉ አብዛኛዎቹ የመስሪያ ሼዶች በስራ ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
መንግስት ባለሀብቶች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለቤት የሚሆኑባቸውን ፓርኮች በመገንባት እና ነጻ የንግድ ቀጣና በመፍጠር ኢንዱስትሪውን የማነቃቃት ስራ ማከናወኑን አመልክተዋል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተከናወኑ ስራዎች አስደማሚ ውጤቶች መገኘታቸውንም ተናግረዋል።
በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የኢንዱስትሪው ዘርፍ 13 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘርፉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
የተፈጠረውን እና የተመረተውን ወደ ተጠቃሚ ለማድረስ የአገልግሎት ዘርፍ ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰው ዘርፉ የኢኮኖሚ እድገት መቋጫና ማሰሪያ እንደሆነም አመልክተዋል።
ፋይናንስን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የአገልግሎት አሰጣጥን በሚያዘምኑ ስራዎች አማካኝነት በርካታ ለውጦች እየመጡ መሆኑን አክለዋል።
ብዝሃ ዘርፎችን ከደጋፊ መስኮች ጋር አጣምሮ በመስራት ብዝሃ ውጤት እየተገኘ እና እድገት እየመጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025