
ባህርዳር፤ግንቦት 30/2017(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል አርሶ አደሮች በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በመስኖ በማልማት እያገኙት ያለው ምርት ከፍጆታቸው አልፎ በመሸጥ ሀብት እንዲያፈሩ እያገዛቸው መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወቅት በመጀመሪያው ዙር መስኖ ከለማው ማሳ ከ30 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ከተሰበሰበው ውስጥም ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታሉ የስንዴ ምርት መሆኑ ተመልክቷል።
አርሶ አደር ሃብቴ አበራ በአዊ ዞን የጓጉሳ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ቀደም ሲል ጀምሮ በበጋ መስኖ ልማት ላይ በመሳተፍ ያገኙትን ምርት ከፍጆታቸው የተረፈውን በመሸጥ በከተማ መኖሪያ ቤት ገንብተው ቋሚ ሃብት ማፍራታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ያገኙትን ጥቅም በማስፋትም ዘንድሮ ሁለት ሄክታር የሚጠጋ መሬት በስንዴ፣ሽንኩርት፣ድንችና ቀይ ስር በማልማት 162 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ የጓንጓ ወረዳ አርሶ አደር አርሶ አደር ጥላሁን ካሳሁን በበኩላቸው፤ ያላቸውን ከሩብ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ሽንኩርት አልምተው ያገኙትን 20 ኩንታል ምርት ለመሸጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የሽንኩርት ምርት ዋጋ ጥሩ በመሆኑ ሰሞኑን የሰበሰቡትን ምርት በተሻለ ዋጋ ሸጠው ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
የምናከናውነው የበጋ መስኖ ልማት የምግብ ፍጆታችንን አሟልተን ተጨማሪ ሃብትና ጥሪት እንድናፈራ ረድቶናል ያሉት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን የደራ ወረዳ አርሶ አደር አዳሙ ሞላ ናቸው።
በየዓመቱ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመንና የበቆሎ ሰብል በማልማት የሚያገኙት ምርት ከፍጆታቸው አልፎ ለገበያው አቅርበው በመሸጥ ሀብት እንዲያፈሩ እያገዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮው በጋም በአንድ ሄክታር ተኩል መሬት ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ስንዴ በማልማት 93 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ጠቁመው፥ከዚህ ውስጥ 70 ኩንታሉን በተሻለ ዋጋ መሸጣቸውን አስታውቀዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የመስኖና ሆልቲ ካልቸር ልማት ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው፤ በክልሉ በመጀመሪያው ዙር መስኖ 330 ሺህ 900 ሄክታር መሬት መልማቱን ተናግረዋል።
አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አርሶ አደሮች በማሳተፍ በተካሄደው የመስኖ ልማት 47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን 30 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ከተሰበሰበው ምርት ውስጥም ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታሉ የስንዴ ምርት መሆኑን አመልክተዋል።
በሁለተኛ ዙር መስኖ ልማት ደግሞ በተለያየ አትክልትና ሰብል እየለማ ካለው 113 ሺህ ሄክታር መሬት 15 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ከክልሉ ግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፥ባለፈው ዓመት የበጋ ወቅት በክልሉ በሁለት ዙሮች በመስኖ ከለማው 299 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ 43 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል።
ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዝያ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በወላይታ ሶዶ ከተማ ከነዳጅ እጥረት ጋር በተያያዘ በህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የነበረውን ክፍተት ለማረም...
Apr 30, 2026
ጅማ፤ ሚያዝያ 21/2018(ኢዜአ)፦ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎቻቸውን ከቀጣናዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማስተሳሰር ዘላቂ ሰላምና የጋራ እድገት ለ...
Apr 30, 2026
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦የትራንስፖርት አገልግሎትን ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ ተግባራዊ የተደረጉ ስልቶች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የትራን...
Apr 29, 2026
ሀዋሳ ፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡-ሀዋሳ ከተማን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል በማድረግ ከተማዋ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ እንድትሆን ርብርብ እየተደረ...
Apr 20, 2026