የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀቶች አመዳደብ ላይ የአሰራር ስርዓት በማሻሻልና ድጋፍና ክትትል በማድረጉ ውጤቶች ተመዝግበዋል

Jun 10, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2017(ኢዜአ)፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀቶች አመዳደብ ላይ የአሰራር ስርዓት በማሻሻልና ድጋፍና ክትትል በማድረጉ ውጤቶች እንዲመዘገብ ማስቻሉ ተገለጸ።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተዘጋጀው ውስን ዓላማ ባላቸው የድጎማ በጀቶች ትልልፍና በጋራ ገቢዎች ክፍፍል ላይ ያተኮረ የፌዴራልና የክልሎች ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ በውስን ዓላማ የድጎማ በጀቶች ትልልፍ እንዲሁም በከፍተኛ ማዕድን አምራች ድርጅቶች የሚገኙ የሮያሊቲ ገቢዎች ክፍፍል ላይ የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በዚሁ ወቅት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የክልሎች የበጀት ድጎማና የገቢ አሰባሰብ ላይ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸው ነው የተነሳው።

በተለይም ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀቶች ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአሰራር ስርዓቱን በማሻሻል እያደረገ ያለው ድጋፍና ክትትል ለውጤቱ መመዝገብ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን በዳሰሳ ጥናቱ ተመላክቷል።

ይሁን እንጂ የውስን ድጎማ በጀቶች ላይ ያለው የትግበራ ሂደት ወጥ በሆነ መንገድ እየተመራ እንዳልሆነ የዳሰሳ ጥናቱ ግኝት ያሳያል።

በጋራ ገቢዎች ክፍፍል ላይ የግልጸኝነት አሰራሩ የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባ የየክልሎቹ ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች አንስተዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሊዳሞ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይገኙበታል።

እነርሱ እንደሚሉት ባለፉት ዓመታት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል።

ውስን ድጎማ በጀት ክፍፍሎች በተቀመጠላቸው ህጋዊ አሰራር መሰረትና መሰረታዊ የህዝቦች ጥያቄን ሊመልስ በሚችል አግባብ መመራት እንዳለባቸውም አንስተዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የደቡብምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተዘጋጀው ውስን ዓላማ ባላቸው የድጎማ በጀቶች ትልልፍና በጋራ ገቢዎች ክፍፍል ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።

ፍትሃዊ የበጀት ክፍፍልን የበለጠ ለማጠናከር መሰራት እንዳለበትም አንስተዋል።

በመድረኩ ለተነሱ የግልጽኝነት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ እና የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ ናቸው።

እንደ ገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጻ፤ ባለፉት ዓመታት ለክልሎች የሚመደበውን በጀት ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች ቢኖሩም የበለጠ ሰፊ ስራ መስራት ያስፈልጋል።

በተለይም በግልጸኝነት፣ በተጠያቂነትና የመረጃ አሰጣጥ ሰርዓት ላይ ቅንጅታዊ አሰራሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፤ ለማዕድን ዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለክልሎች የጋራ በጀት ክፍፍል ትኩረት አለመሰጠቱን ተናግረዋል።

ይሁንና በአሰራሩ መሰረት በከፍተኛ ማዕድን አምራች ድርጅቶች የሚገኙ የሮያሊቲ ገቢዎች ክፍፍል ላይ ሁሉም ክልሎች በሚደርሳቸው ልክ ማግኘት እንዳለባቸውና እዚህ ላይ ያሉ ከፍተቶችን በፍጥነት ለማረም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሽመልስ አብዲሳ፤ በውስን ድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል በተቀመጠላቸው ቀመር መሰረት ግልጽ አሰራርን ተከትለው ሊተገበሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በሰጡት ማጠቃለያ ለክልሎች በሚከፋፈለው ሀብት ፍትሃዊነት ላይ ምንም አይነት ጥያቄ አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

ይሁንና በውስን ድጎማ በጀትና በጋራ ገቢ ክፍፍል ላይ የተዘረጉ አሰራሮችን በግልጽነት ከመተግበር አኳያ ያሉ ክፍተቶችን ባለደርሻ አካላት በቅንጅት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.